በገቢዎች ቢሮ ስም ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ግ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በገቢዎች ቢሮ ስም ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ነን በሚል ስም የንግድ ተቋማትን ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።

ተጠርጣሪዎቹ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ በንግድ ቤቶች በመዞር ያለደረሰኝ ግብይት ፈጽማችኋል በሚል 100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው በመግለጽ፣ ቅጣቱን ለመንግስት ከመክፈል ይልቅ ለእነሱ 50 ሺህ ብር እንዲከፍሉ በመጠየቅ ሲያጭበረብሩ ነበር።

ግለሰቦቹ እውነተኛ ማንነታቸውን በመደበቅና ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ወንጀሉን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓርቲ ንጉሴ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አቶ ምትኩ ጋዲሰ በሐሰተኛ ስም አየለ ጥላሁን፣ እንዲሁም አቶ ጌታሁን ደቻሳ በሐሰተኛ ስም አድማሱ ከበደ በሚል ማንነታቸውን በመቀየር የሐሰት መታወቂያ ተጠቅመው ሲያጭበረብሩ በንግዱ ማህበረሰብ ጥቆማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። 

በአሁኑ ወቅትም በሕግ አግባብ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አቶ ፓርቲ አስረድተዋል።

በተጠርጣሪዎቹ እጅ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ሐሰተኛ መታወቂያ ብቻ ሳይሆን የመሬት ባለሙያ መሆናቸውን የሚገልጽ ሌላ ሐሰተኛ መታወቂያም መገኘቱን ገልጸዋል።

ከዩኒፎርም ውጪ ቁጥጥር የሚያካሂዱ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ባርኮድ ያለው መታወቂያ የሚይዙ በመሆኑ፣ ግብር ከፋዮች መታወቂያቸውን በመጠየቅና ባርኮዱን በስልክ ስካን በማድረግ ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የንግዱ ማህበረሰብ በገቢዎች ቢሮ ስም የሚፈጸሙ ማጭበርበሮችን ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት ወይም ለቢሮው በተዘጋጀው 7075 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ አበባ  ገቢዎች ቢሮ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.