ኢትዮጵያ የፀናቸው በፈተናዎች ውስጥ አልፋ ነው!...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ኢትዮጵያ የፀናቸው በፈተናዎች ውስጥ አልፋ ነው! ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀችው በፈተናዎች ወስጥ አልፋ ነው። ኢትዮጵያ በተደራጁ ሰራዊቶቿ፤ የተባበረ ልብ ባላቸው ህዝቦቿ እንዲሁም ዋጋ ለመክፈል በማይሰሰቱ ልጆቿ አማካኝነት ፈተናዎችን ተሻግራ ስሟን አጽንታ ይዛለች። #የጠሚሩምላሾች #PMOEthiopia

መከላከያ ሠራዊትን በሚመለከት

መከላከያ እንደ ቤት ነው። መከላከያን ብቻውን ብንገነባ አይዘልቅም። ኢኮኖሚው እሱን የሚሸከም መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል። መከላከያ በአንድ ምሶሶ መቆም አይችልም። ሁሉም ምሶሶዎች መገንባት አለባቸው። እነዛ ምሶሶዎች ደግሞ የአየሩም፣ የምድሩም የቴክኖሎጂውም ነው። በዚህም በመከላከያ ስትራቴጂ አማካኝነት በሁሉም ምሶሶዎች ሸብረክ የማይል ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ ነው። መከላከያ ቴክኖሎጂን በሚገባ የሚጠቀም ተቋም አድርገነዋል። ይህም በውጤቱ እየታየ ነው።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም ራሷን እንደታላቅ ወንድም በመቁጠር እየሰራች ነው። ይሄ ደግሞ እንዲሁ የሚነገር ሳይሆን በሩዋንዳ፣ በሶማሊያ ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ ፣ በደቡብ ሱዳን ተሰልፈን ሞተን በተግባር ያሳየነው ነው። አባቶቻችን አድርገውታል፤ እኛም አድርገነዋል። ይህን በጎ ስራ ለመድገም ነው የምንዘጋጀው።

ኢትዮጵያና ድል!

ኢትዮጵያ በታሪኳ የትኛውንም ሀገር በመውረር አትታወቅም። ወደፊትም ያ ፍላጎት የላትም። ሌሎች ማወቅ ያለባችው ግን ትንሽም ይሁን ትልቅ። ማንም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መጥቶ ኢትዮጵያን ወርሮ በክብር መመለስ አይችልም። ይሄ በጂኦግራፊ የታጠረ ጉዳይ አይደለም። ማንም ነው ያልኩት። አድዋ ይደገማል፤ አትሞክሩን!

ሠላምና ይቅርታን በሚመለከት

በንግግር በሠላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት የስልጣኔ ምልክት ነው። ታጋሽነት፣ ቻይነትና ይቅር ባይነትን መላበስ ለሀገር ግንባታ በእጅጉን ያግዛል። ሠላምን የምናስቀድመው የአንድ ቀን እረፍት ለእናቶች ያለውን ጥቅም ስለምናውቅ ነው። ስለ ሀገር የሚከፈል ዋጋ መረር ያለ እውነትን መቀበል ይፈልጋል፤ ከዛ ውስጥ አንዱ ይቅርታ ነው። ይቅርታን የምናስቀድመውም ንግግርና ሰላም ለኢትዮጵያም ለቀጣናውም እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ ነው።

ኢትዮጵያን ማወክ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች

“ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” በሚል ስጋት ኢትዮጵያን ለማወቅ የምትፈልጉ ሁሉ፤ ባቄላዋ አድራለችና ከእንግዲህ አትቆረጠምም፤ መተው ነው የሚሻላችሁ! ገና ካደረች የሚል ሳይሆን አሁን አድራለች!

በትጥቅ ለሚንቀሳቀሱ አካላት መልዕክት

መንግስት ራሱን ለማቆየት ሳይሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ጨክኖ የሚሰራ ነው። እናንተ በያዛችሁት መንገድ መቼውም አይሳካም። ከእናነት በላይ አሻግሮ የሚያቅድ መንግስት ነው። ስለዚህ ይብቃችሁ ተመለሱ ወደ ሠላም ብትመለሱ ይሻላል ነው መልዕክቴ!

የትግራይ ክልልን በሚመለከት

የትግራይ ሕዝብ ትጉ ሰራተኛ ነው፤ ሰላም ወዳድ ነው ግን እድል አላገኘም። በከፍተኛ ሁኔታ ወጣቶችን እየገበሩ እድሜያቸውን የሚያቆዩ ሰዎች ተፈጥረውባቸው ቆይተዋል። እነዛ በሰላም ጊዜ የሚፎክሩ ሰዎች አስገዳይ እንጂ ሟች አይደሉም። አትግራይ ሕዝብ አሁን በሚገባ ነቅቷል።ወደ ሠላማዊ ጉዞው ተመልሷል። በዚህ ውስጥ የእኛ ተግባር የተሟላ ሰላም መመለስ፤ መሰረታዊ አገልግሎት መመለስ፤ የትግራይ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር ምርጫ በፍጥነት ማካሄድና የተቸገሩትን ደግሞ ማገዝ ነው።

ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ

በምክክሩ ህገ-መንግስቱን በሚመለከት የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሕግ ባለሙያዎች ላላፉት ወራት ቀን እና ማታ ሲሰራ ቆይቷል። በሚቀጥሉት ጊዜያትም ይህ ጉዳይ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል። የእኛ አቋም አራት ዓመት የተለፋበት እያንዳንዱ ሃሳብ መተግበር አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለን። በዚሁ መንገድ የሚፈጸም ይሆናል።

ታላቁ የመደመር ስትራቴጂን በሚመለከት

ታላቁ የመደመር ስትራቴጂ፤ ከመንግስት የሚሻገር፤ ከትውልድ የሚሻገር የስልጣኔ ጉዞ ያስፈልጋል በሚል የተዘጋጀ ነው። በቅድሚያ ኢትዮጵያ ሃብታም ናት፤ ዜጎቿ ደግሞ ደሃ ናቸው። ይህን እንዴት መቀየር ይቻላል የሚለውን አጠናን። ሁለተኛ የት መድረስ እንፈልጋለን የሚሉውን የሚቀይሩ ግቦቻችን አስቀመጥን። ሶስተኛ በምን አቅም ነው እዛ የምንደርሰው የሚለውን ይዟል። አቅጣጫችንንም ጥርት አድርጎ ያሳያል። ልማት ከመጣ በኋላ ደግሞ እንዴት እናስተዳድረዋለን የሚለውንም አስቀምጧል። ይሄን ለማድረግ ሀገር የሚገነባባት 15 ሞዴሎች ተቀምጠዋል። ያንን ደግሞ በሃይል ቬክተር አማካኝነት ወደ ብሔራዊ ሃይል ይቀየራሉ። ብሔራዊ ሃይል ደግሞ በኢኮኖሚ አርክ አማካኝነት ካፒታልን ለማምጣትና ለማስተዳደር ይውላል። ስልጣኔን የምንገነባው ለትውልድ ነው። በእኔ እምነት የልጅ ልጆቻችን መሰረቱን ይረግጣሉ። ልጆቻቻን ደግሞ ምሶሰውን ይይዛሉ። የእኔ እና እናንተ ስራ እየገነባን ጣሪያ ላይ መቀመጥ ነው። ይሄ ገንቢ ትውልድ ነው። የሚጠቀሙት ልጆቻችን ናቸው።ለመገንባት መታደል ጥሩ ነገር ነው። ገንብቶ ማሸጋገር ግን ጥበብ ይፈልጋል።

ሰዎች ወደ ሁርሶ የሚገቡት ለውጊያ ብቻ ሳይሆን ሰው ለመሆን፣ ሀገርን ለመውደድ እና ባንዲራን ለማክበር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

****************

የሁርሶ ሥልጠና ዋና ዓላማ ባለሥልጣናትንና ትውልድን ለአገልግሎት፣ ለዲሲፕሊንና ለኢትዮጵያ ፍቅር ማብቃት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሰው ሲሾም ጠባዩ ሊቀያየር እንደሚችል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሥልጠናው ይህን ለመቀየር ያግዛል ብለዋል።

ሠልጣኞች መሬት ነክተው፣ አልጋ አንጥፈው፣ አንሶላና ካልሲ አጥበው እንዲለማመዱ የሚደረገውም አገልጋይ እንዲሆኑ ተፈልጎ እንደሆነ አብራርተዋል።

በሥልጠናው ወቅት ሁርሶን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ ሚኒስትሮችና ሠልጣኞች ከዚህ ቀደም ያልለመዷቸውን ቀላል የሚመስሉ ኃላፊነቶች ሲወጡ ራሳቸውን እንደፈተሹ ጠቁመዋል።

አንድ ሰው በሹመት ወቅት "ትልቅ ሰው ነኝ" ብሎ ቢያስብም፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወይም ቀላል ሥራዎችን በትክክል በመሥራት ሲፈተን "የማልችለው ነገር አለ" የሚለውን እውነት እንደሚገነዘብ አንስተዋል።

ይህም የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ የትዳር አጋሮችንና ሠራተኞችን ለማክበርና በጋራ ለማደግ የሚያግዝ የ"መደመር" እሳቤን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤት አባላትና ወላጆች ልጆቻቸውን በክረምት ወራት ለ15 ቀናት ወይም ለአንድ ወር ወደ መከላከያና ወደ ሥልጠና ማዕከላት እንዲያስገቡ መክረዋል።

ሀብት መኖር በራሱ ለልጆች ፈተና ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም፣ ሥልጠናው ዲሲፕሊን ያለው፣ ጠዋት የሚነሳ፣ በትብብር የሚያምንና የወደቀ ወንድሙን ለማንሳት የሚቀዳደም ትውልድ ለመፍጠር ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የሚኒስትሮች ሥልጠና የውትድርና ሳይንስንና አመራርን በተወሰነ ደረጃ በመረዳት ኢትዮጵያን በኃላፊነት ለመምራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በማጠቃለያቸውም የሁርሶ ሥልጠና በአንዳንድ ሀገራት ካለው አስገዳጅ የውትድርና ዝግጅት ጋር እንደማይመሳሰል አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዋናው ዓላማ ሰዎችን ለውጊያ ማዘጋጀት ሳይሆን ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ሀገር የሚወዱና አገልጋይ "ሰው" ማድረግ በመሆኑ ከሌሎች ሀገራት ልምድ ጋር ማቀራረብ ተገቢ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

ኤርትራን በተመለከተ

የኤርትራ መንግስት ከተደበቀበት ወጥቶ ከማያውቅበት በራሳችን አውሮፕላን እየወሰድን ጎረቤት ጋር አገናኝተነዋል። ይህን ያደረግነው በጋራ ማደግ እንደምንችል ስለምናምን ነው። ከኤርትራ መንግስት አብረን ለመልማት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። ለምሳሌ ኤሌክትሪክ ስለሚቸገሩ እናስገባላችሁና በኢትዮጵያ ዋጋ ተጠቀሙ ብለናቸው ነበር። ነገር ግን የኤርትራ መንግስት አልፈለገም።መንገድ፣ ወደብ በጋራ እንስራ ብለን ጠይቀን የኤርትራ መንግስት አልፈለገም። ምክንያቱ ደግሞ የኤርትራ መንግስት ለጊዜው መንግስት ነው። ነገር ግን ልማት፣ እድገት የሚል ቋንቋ መዝገበ ቃላቱ ውስጥ የለውም። ልማት ፈጽሞ አይገባቸውም። ይሄ የእነሱ ድክመት ነው። ሰሜን እዝ ሲጠቃ ያሳዩት የመልካም ጉርብትና ባህርይ ደግሞ ይመሰገናል። ነገር ግን ችግሩ የተጀመረው ወደ ትግራይ በመግባት ወጣቶችን መግደል፣ መሰረተ ልማት ማውደምና መዝረፍ ሲጀምሩ ነው። በመጨረሻም የፕሪቶሪያው ውል ሲፈረም የኤርትራ መንግስት ማኩረፍ ጀመረ። አሁን ከኤርትራ መንግስት የምንፈልገው ሁለት ነገር አለ። አንዱ የኢትዮጵያን ጠላት ማስታጠቅ፣ ማስታጠቂያ መስመር መሆን፤ ለኢትዮጵያ ጠላቶች መተባባበር አቁሞ። ሁለተኛው ደግሞ ለጋራ ልማት አብረን እንስራ። አብረን ስንሰራ ሃሳቡን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን እኛ እናዋጣለን። ተባባሪ ብቻ እንድትሆኑ ነው የምንፈልገው። ይህን ማድርግ ከቻላችሁ በሰላም አብሮ መኖር ይቻላል። ነገር ግን ሻዕቢያ በማይታረም ስህተት ውስጥ የሚዳክር ሃይል ከሆነ ጥፋቱ ለኤርትራ ነው የሚሆነው።

 

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.