ከ40 ዓመታት በኋላ የሚሰጥ እውቅና አክብሮቱ ለታሪክ፣ ተግባሩ እውቅና ሰጪውን የሚያስከብር ነው፡- የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ
ከሰሞኑ በተመረቀው የቦሌ ኮሪደር ልማት ውስጥ በአደይ አበባ ስታዲየም ጎን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አባት ለሆኑት ለአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ሀውልት መቆሙ ትውልዱ ስራቸውን እንዲያውቅና እንዲነሳሳ የሚያደረግ መሆኑን የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ገልፀዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ሰርተው ያገለገሉ ሰዎች እንዳይዘነጉ ምልክታቸውን በማስቀመጥ የሀገር ስም ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው የመታሰቢያ ሃውልቱ ብዙ ህዝብ በሚሰባሰብበት እና በሚያምር ስፍራ በመገንባቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ላለፉት 40 ዓመታት ሳይረሱ የቆዩ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ከትውልድ ትውልድ እየተረሳ ስለሚሄድ እንደዚህ ያለ ቋሚ መታሰቢያ መቆሙ ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህንን የመታሰቢያ ሃውልት ታሪክን ያከበረና ደግነት የተሞላበት መሆኑን አንስተዋል። አንድ ሰው በህይወት ካለፈ ከ40 ዓመታት በኋላ የሚሰጥ እውቅና አክብሮቱ ለታሪክ መሆኑን፣ ተግባሩ እውቅና ሰጪውን የሚያስከብር እና ሌሎች በየዘርፉ እንዲተጉ የሚያበረታታ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የመታሰቢያ ሀውልቱ መቆም በእግር ኳስ አፍቃሪያን በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረው ደስታ እንዳስደሰታቸውና ኩራት እንዲሰማቸው ማድረጉን አመልክተዋል።
ሃውልቱ የፍላጎት መነሳሳትን እንደሚፈጥርና በተለይም ሰነዱንና ታሪኩን በያዙት ላይ ከባድ ሃላፊነት እንደሚጥል አቶ ታደለ ገልፀዋል።
አቶ ይድነቃቸው በፍቅር ብቻ ተነሳስተው በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች ከባዶ ተነስተው የስፖርት ኮሚሽን በማቋቋም ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከባቸውን አቶ ታደለ አንስተዋል።
አቶ ታደለ ለሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎች የማስታወስና እውቅና የመስጠት ተነሳሽነት ላላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ እና ለሌሎች የመንግስት አመራሮች ሃውልቱ የተገነባበትን ውብና ህዝብ የሚሰባሰብበት ቦታ በመምረጣቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.