ኪነ ጥበብ የጋራ ትርክት : የትዉልድ እና የሃገር ገጽታ መገንቢያ መሳሪያ ነዉ
ኪነ ጥበብ በአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ልማትና ዕድገት ውስጥ ያለው ሚና የጎላ ነው፡፡
የህብረተሰብን ነባራዊ ሁኔታ፣ ታሪክ፣ እሴት እና ህልም የሚያንጸባርቅ መስታወት በመሆኑ የለውጥና የዕድገት ዋንኛ የማነቃቂያ ኃይል ነው፡፡
ልዩነቶችን በማጥበብ በህዝቦች መካከል ፍቅር፣ መቻቻል እና አብሮነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን እንዲያከብሩ እና እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ በማድረግ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ሀገር እንድትኖር ያግዛል።
የሰዎችን ጭንቀት ያስታግሳል፣ አእምሮን ያዝናናል፣ ፈጠራን ያዳብራል፣ ወጣቶች ኃይላቸውንና አቅማቸውን በአዎንታዊ መንገድ ወደ ፈጠራ ሥራ እንዲያመሩ ያነሳሳል፡፡
ስለ ሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ እና ብሔራዊ አንድነት ግንዛቤን በመፍጠር ጤናማ ማህበረሰብ እንዲገነባ ያደርጋል፡፡
ኪነ ጥበብ በሙያዊ ሥነ ምግባር፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት፣ በኀገር ክብርና ፍቅር መርህ የማይመራ ከሆነ ለሰላም መደፍረስ፣ ለልማት እጦትና ለድህነት ትልቅ መንስዔ ይሆናል፡፡
ሀሰተኛና ከፋፋይ ትርክቶች እንዲስፋፉ፣ የህዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲላላ፤ ጽንፈኝነትና ህገወጥነት እንዲባባስ፣ የሀገር ሰላም እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ፣ ግጭትና ጦርነት እንዲፈጠር ትልቅ ምክንያትም ይሆናል፡፡
ኪነ ጥበብ የሀገርን ቁሳዊ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ የህብረተሰቡን መንፈሳዊና ስነ-ልቦናዊ ልማት በመምራት የዕድገቱ ዋነኛ ምሰሶ ይሆናል።
በርካታ የዓለም ሀገራት ሙዚቃን፣ ስዕልን፣ ቴአትርን፣ ፊልም እና ሥነ-ጽሁፍን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም የዜጎቻቸውን አመለካከት ከመቅረጽ ባለፈ ጠንካራ ሀገር መፍጠር እና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ሀገራቱ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ፋሽን፣ እደ-ጥበብ እና ቱሪዝምን በማቀናጀት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ ዋንኛ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርገውታል፡፡
የሀገራቸውን ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ቱሪስቶችን ለመሳብም ተጠቅመውበታል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ በርካታ ጸጋዎችን፣ እውቀቶችን እና ተሰጥኦዎች ያላት ሀገር ናት፡፡
በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሙዚቃ፣ በስዕል፣ በቴአትር፣ በፊልም እና ሥነ ጽሁፍ ስለ ሀገራቸው አንድነትና ነጻነት፣ ስለ ህዝቦች አብሮነት፣ ስለ ልማት፣ ስለ ሰላምና ስለ ሥራ ፈጠራ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ለህዝብ አበርክተዋል፡፡
ከያኒያኑ ኪነ ጥበብን እና ባለሞያዎችን የሚያበረታታ እና የሚደግፍ ቴክኖሎጂ፣ ግብአቶች፣ ድጋፍና ፖሊሲ በሌለበት በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ካሏት ጸጋዎች አንጻር በአፍሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ መፍጠር የሚችል ሀገራዊ አቅም መገንባት አልተቻለም፡፡
በሀገር ደረጃም ቢሆን ሙዚቃን፣ ስዕልን፣ ቴአትርን እና ስነ ጽሁፍን በመጠቀም የጋራ ትርክትን ከመፍጠር፣ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት እና ብሔራዊ ጥቅምን ከማረጋገጥ ረገድ በርካታ ውስንነቶች እንደነበሩ የዘርፉ ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡
ሞያውን ላልተገባ አላማ የሚጠቀሙ ጥቂት ከያኒያን እና ሌሎች ግለሰቦች የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት የሚንዱ፣ ልዩነትንና ጥላቻን የሚፈጥሩ፣ ከእንስራና ከእንደግ ይልቅ ጦርነትንና መገዳደልን እንጀግንነት የሚያሞካሹ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጥሱ፣ የሀገርን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ነጠላና ከፋፋይ መልእክቶችን ሲያስተልፉ እንደነበረ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ዛሬም ቢሆን ከልማት፣ ከሰላም፣ ከህብረ ብሔራዊ አንድነት እና ከህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይልቅ፣ የልዩነትና የመከፋፈል መንስኤ የሆኑ ነጠላና ሃሰተኛ ትርክቶችንና መልእክቶች የሚያስተላልፉም አሉ፡፡
ኪነ ጥበብ የሀገር መገንቢያ ኃይል መሆኑን የተረዳው የመደመር መንግሥት፣ ከለውጡ ወዲህ ስብራቶቹን በመጠገን፣ አስቻይ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን በማውጣት ዘርፉን በማበረታታ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ የሲኒማ እና ቴአትር ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፣ በቱሪዝም ዘርፍ፣ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት የተገነቡ ፓርኮችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ኪነ ጥበብን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ቅርሶች፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሌሎች ጸጋዎች ለኪነ ጥበብ በተለይም የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ ማሳደግ የሚችሉ ናቸው፡፡
ሃገራቸዉን በጀግንነት ላገለገሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመዲናዋ የተገነቡት የመታሰቢያና የክብር ሃዉልቶችም አዲሱ ትዉልድ ከታላላቆቹ እንዲማር ታቅደዉ የተሠሩ ናቸዉ።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.