ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረጊያ አንዱ እና ዋናው ቁልፍ ሥራችን የሚሆነው የቤት ግንባታ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እና የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 100 ሺሕ ቤቶችን በተለያዩ አማራጮች ወደ ግንባታ ማስገባቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ይህ አፈጻጸም በብሔራዊ ደረጃ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የተያዘውን የጉባ ብስራት እቅድ መነሻ በማድረግ የተከናወነ ሲሆን፣ በከተማዋ ታሪክ በአንድ ዓመት ውስጥ በዚህ ደረጃ በስፋት የቤት ግንባታ ሲጀመር የመጀመሪያው መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በጀት እየተገነቡ ካሉ 50 ሺህ ቤቶች መካከል ግማሽ ያህሉ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ነው ከንቲባ አዳነች የጠቀሱት።
በተለይም እንደ ቱሉ ዲምቱ ባሉ ሳይቶች 10 ሺሕ ገደማ ቤቶች ለርክክብ እየተዘጋጁ መሆኑን እና ቀሪዎቹም በ24 ሰዓት የሥራ መርሐ ግብር እየተፋጠኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጓዳኝም በመንግሥት እና በግል አጋርነት (PPP)፣ በማኅበራት እንዲሁም ለመምህራን፣ ለጤና ባለሙያዎችና ለፖሊስ አባላት የተጀመሩ ሌሎች 50 ሺሕ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መገኘቱን ጠቁመዋል።
እየተገነቡ ያሉት ቤቶች ለልማት ተነሺዎች፣ ለዓመታት ቆጥበው ለሚጠባበቁ ነዋሪዎች በዕጣ የሚተላለፉና ለኑሮ አስቸጋሪ ከሆኑ አካባቢዎች ተነስተው በዚያው መልሰው ለሚሰፍሩ ነዋሪዎች ቅድሚያ የሚሰጥባቸው ናቸው።
ከንቲባዋ አክለውም ባለፉት ዓመታት የነበረውን የቤት አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ነዋሪዎች ቁጠባቸውን በማሳደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.