ሚድያዎች ምንጩ ያልታወቀና ያልተረጋገጠ የተዛባ መረጃ ኃላፊነት በጎደለዉ አግባብ ከማሰራጨታቸዉ በፊት ከትክክለኛዉ እና ኃላፊነት ከተጣለበት አካል መረጃ መጠየቅ ይገባቸዋል። መረጃ የማግኘት መብትም አላቸዉ ።
አዲስ አበባ በፈጣን የልማት ጉዞ ላይ ነች። ከተማዋ እያስመዘገበች ያለችውን የልማት እድገት ዓለም አቀፍ ተቋማት በራሳቸዉ መንገድ መረጃ እና ማስረጃ ሰብስበዉ ካረጋገጡ በኃላ እየተደነቁ እዉቅና እየሰጧት ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በመረጃ እና ማስረጃ በቀላሉ ማረጋገጥ ሲችሉ እውነታውን ወደ ጎን በመተው ኃላፊነት በጎደለዉ አግባብ አዛብተዉ ያሰራጫሉ።
የከተማ አስተዳደሩ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ሲታዩ የነበሩ የቢሮክራሲ እንግልቶችን፣ የአሠራር መዘግየቶችን፣ ሕገ-ወጥ ደላላነትንና ለብልሹ አሠራር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ክፍተቶችን ለማስወገድ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች አከናውኗል። ሪፎርሙም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እንግልት መቀነስ ያስቻለ ከመሆኑም ባሻገር፣ የሕዝብና የመንግስትን ውስን ሀብት ከብክነትና ከሕገ-ወጥነት ለመጠበቅ አስችሏል።
✅ ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የፎርቹን ጋዜጣ በህትመቱ ኃላፊነት በጎደለው አግባብ የተዛባ መረጃ ካሰራጨ እና ብዙዎች እንዲወዛገቡ ካደረገ በኃላ መሳሳቱን ሲያዉቅ አርሟል።
ስህተትን አመኖ እርምት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ የመረጃዎችን ትክክለኛነትና ታአማኒነት አስቀድሞ ከምንጩ ማረጋገጥ ተገቢ ነው።
በቅርቡ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባሳለፈው ውሳኔ የተወሰኑ ነባር አሠራሮች የነበሩባቸውን ሂደት ማሳጠር እንጂ ከመሬት አሰጣጥ ደንብ ፣ወይም መመሪያ አልወጣም።
ነገር ግን በሰነድ አልባ መሬትና በካቢኔ የተወሰኑ የመሬት ጉዳዮችን የማከፋፈል ኃላፊነትን ከዚህ ውሳኔ ጋር በማያያዝ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ከውሳኔው ይዘት ጋር የማይገናኝ እና ሕብረተሰቡን ሊያደናግር የሚችል ነው።
✅ የውሳኔው ዋነኛ ዓላማ፦ እንግልት እና መዘግየትን መቀነስ ነዉ!
ከውሳኔው ዋነኛ ይዘቶች አንዱ አንድ ሕጋዊ ይዞታ ወደ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ይዞታ እንዲከፈል የሚቀርብ ጥያቄ የካቢኔ ስብሰባን መጠበቅ ሳያስፈልግ አሳማኝ ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥምና በመሬት አስተዳደር ቢሮ ተረጋግጦ ሲቀርብ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፀድቆ እንዲፈጸም የሚያስችል አሠራር ነው።
ይህ አሠራር የተዘጋጀው ዕለት ተዕለት ለሚከናወኑ መደበኛ የመሬት አገልግሎቶች ሳይሆን፣ አልፎ አልፎ በግለሰቦች ወይም በባለመብቶች ጥያቄ ሲቀርብና ሲያጋጥም በጥንቃቄ የሚተገበሩ ውስን ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከት ነው። ምክንያቱም ሕጋዊ ይዞታዎችን ያለበቂ ምክንያት መከፋፈል የሕዝብን ሀብት ለሕገ-ወጥ ተግባርና ለግል ጥቅም ለማዋል የሚያስችሉ ክፍተቶችን ሊፈጥር ይችላል።
ስለዚህ በዚህ ዓይነት ውሳኔዎች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ የግለሰቦችን መብት ለመጠበቅ፣ ሕገወጥ የመሬት ንግድን ለመከላከልና ተገልጋዮች በሕጋዊው መንገድ ብቻ ያለ አላስፈላጊ እንግልት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የተወሰደ ማሻሻያ ነው።
✅ የተዛባ መረጃ ሕብረተሰቡን እንዳያደናግር!
በዚህ ሁኔታ የአሠራሩን ይዘት በማዛባት፣ በተሳሳተ መንገድ በማቅረብና ያልወጡ ደንቦችን እንደወጡ በማስመሰል የሚሰራጩ መረጃዎች ተገልጋዩን ለግራ መጋባትና ላላስፈላጊ እንግልት ሊዳርጉ ስለሚችሉ ለወደፊቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ እናሳስባለን።
በተለይም የመሬት አስተዳደርን በተመለከተ በሕጋዊ መረጃ ፋንታ በወሬና በደላላ ትርክት ላይ ተመስርቶ መንቀሳቀስ ሕብረተሰቡን ለተጨማሪ ወጪ፣ ለጊዜ ብክነትና እንግልት ይዳርጋል። ስለዚህ ማንኛውም የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ሲኖር በተቋሙ የሚሰጡ ግልጽ ማብራሪያዎችን መከታተል ወይም ከሕጋዊ የመንግሥት የመረጃ ምንጮች ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
✅ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የሚሰራው ሪፎርም የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው!
ስለዚህም ሕብረተሰቡም በተዛቡ መረጃዎች እንዳይደናገር፣ በደላሎች ተጽዕኖ ሥር እንዳይወድቅና ማንኛውንም ጉዳይ በህጋዊ መንገድ እንዲያስፈጽም ጥሪ እናቀርባለን።
የሕዝብ ሀብትን የመጠበቅ ኃላፊነት የአስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ግዴታ ነው።
የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.