የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዓመታዊ የግብር ማሳወቅና ክፍያን በኦንላይን አስጀመረ
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዓመታዊ የግብር ማሳወቅና ክፍያን በኦንላይን አስጀመረ
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ የደረጃ «ሀ» ግብር ከፋዮች ዓመታዊ የግብር ሂሳባቸውን በኦንላይን እንዲያሳውቁና ክፍያቸውን ከሥራ ቦታቸው ሳይንቀሳቀሱ እንዲፈጽሙ የሚያስችል አዲስ አሠራር መዘርጋቱን ገለጸ።
ቢሮው ይህን የገለጸው በአዲስ አበባ የግብር አሰባሰብ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓመታዊ የግብር ማሳወቅና ክፍያ ሂደትን በዲጂታል አሠራር ለማከናወን የተዘረጋውን አገልግሎት በሚመለከት ባዘጋጀው የጋዜጣዊ መግለጫ መድረክ ላይ ነው።
አዲሱ አሠራር የግብር አገልግሎትን ለማዘመን፣ የግብር ከፋዮችን እንግልትና የቢሮ ለቢሮ ምልልስ ለመቀነስ፣ የጊዜና የወጪ ብክነትን ለመታደግ እንዲሁም የግብር ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
በተያያዘም ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የደረጃ «ሀ» ግብር ከፋዮች ወርሃዊ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና የሠራተኞች ደመወዝ ግብር ማሳወቅና መክፈል በኦንላይን እንዲያከናውኑ የሚያስችል አሠራር ወደ ተግባር መግባቱን ቢሮው አስታውቋል።
በዴስክ ኦዲት የሂሳብ መዝገብ ጉድለቶችን ለመከላከል ከግብር ኦዲት ሥራዎች ጋር በተያያዘም ቀደም ሲል በግብር ከፋዮች ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመቅረፍና የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ጉድለቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የዴስክ ኦዲት አፈጻጸም አሠራር መዘርጋቱን ቢሮው ገልጿል።
በተለይም ከባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴና ከዕቁብ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ አሠራሮች መዘርጋታቸው ተጠቁሟል።
ከንግድ ሥራ ውጭ በብድር፣ በውርስ፣ በስጦታና በሌሎች ምክንያቶች የተገኙ ገንዘቦች እንደ ንግድ ትርፍ ገቢ ተቆጥረው ተገቢ ያልሆነ ግብር እንዳይጣልባቸው፣ ግብር ከፋዮች ሊያቀርቧቸው የሚገቡ ሰነዶችና ማስረጃዎች በግልጽ እንዲለዩ መደረጉንም ቢሮው አብራርቷል።
የንግድና የቁጠባ የባንክ ሂሳቦችን መለየት ያስፈልጋል የግብር ከፋዮች ለንግድ ሥራና ለቁጠባ የሚጠቀሙባቸውን የባንክ ሂሳቦች በግልጽ መለየት እንዳለባቸውም ተገልጿል።
ግብር ከፋዮች የባንክ ሂሳቦቻቸውን በአግባቡ ለይተው ሲያቀርቡ፣ በኦዲት ወቅት ለግብር ዓላማ የሚመረመረው የንግድ ሥራ ሂሳብ በግልጽ እንዲለይ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ቢሮው ጠቁሟል። ይህም በባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል።
የዲጂታል አገልግሎቱ ዓላማ በዓመታዊ ግብር፣ በወርሃዊ ቫትና በደመወዝ ገቢ ግብር ማሳወቅ ላይ የተዘረጉት የኦንላይን አገልግሎቶች የግብር ከፋዮችን ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር በአካል የሚያገናኙትን ሂደቶች በመቀነስ ለብልሹ አሠራር የሚኖረውን ዕድል ለመግታት ያግዛሉ ተብሏል።
በመሆኑም ግብር ከፋዮች አዲሱን የዲጂታል አሠራር በአግባቡ በመጠቀም ለስኬታማ ትግበራው የድርሻቸውን እንዲወጡ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
በመጨረሻም የደረጃ «ሀ» ግብር ከፋዮች ያለቅጣት ዓመታዊ ግብራቸውን አሳውቀው የሚከፍሉበት የ2019 ዓ.ም. የጊዜ ገደብ ጥቅምት 30 መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።
ግብር ከፋዮችም የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በኦንላይን በመላክ፣ ተጨማሪ ሰነዶችን በቃለ መሐላ ወቅት ባቀረቡት ኢሜል በመላክና በሚደርሳቸው የክፍያ ማዘዣ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉ አሳስቧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.