70 ግራም ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከዳቦ አምራች ማህበራት ጋር ስምምነት ተደረሰ።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ የዳቦ አምራቾች ማህበር አመራሮችና አባላት ጋር በዳቦ አቅርቦት ዙሪያ ተወያይቷል።
በውይይት መድረኩ ከ70 ግራም የዳቦ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከክብደት፣ ከዋጋና ከጥራት አንፃር የተካሄደ የዳሰሳ ውጤት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በመድረኩ የዳቦ አምራቾች ማህበር አባላት ከስንዴ ዱቄት አቅርቦትና ከብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ እየገጠመን ነው ያሉትን ችግሮች ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ አቅርበዋል።
ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የከተማ አስተዳደሩ ለህብረተሰቡ ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ከማድረግ አንፃር ለዳቦ ፋብሪካዎች ለ10 ዓመት መሬት በነፃ ከመስጠት ጀምሮ፣ በሸገር ዳቦ አማካኝነት ድጎማ የማድረግና ሌሎች የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ በመስራቱ የዳቦን ገበያ ለረጅም ጊዜ አረጋግቶ ማቆየት መቻሉን ገልፀዋል።
ወ/ሮ ሀቢባ አያይዘው በከተማችን የሚገኙ የዳቦ አምራቾች የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ በማድረግ 70 ግራም ዳቦ በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የድርሻቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ወ/ሮ ሀቢባ የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ በቂ የስንዴ ዱቄት አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልፀው የዳቦ አምራቾች ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ ሠራተኞች ሲያጋጥሙ በ8588 ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀው በጥቆማው መሠረት ፈጣንና ተገቢ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በመጨረሻም የዳቦ አምራች ማህበራት አመራሮችና አባላት የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ በማድረግ 70 ግራም ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ይህንንም ለከተማ አስተዳዳሩ በአጭር ጊዜ ለማሳወቅ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.