በትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ይከናወኑ የነበሩ ተግባራት ለትራንስፖርት ቢሮ፣ ለመንገዶች ባለሥልጣንና ለትራንስፖርት ማኔጅመንት ማዕከል ተከፋፍለው ተሰጥተዋል።
በቅርቡ የከተማችን ምክር ቤት በከተማ አስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት የሥልጣንና የተግባር ክፍፍልን ለመወሰን ባጸደቀው አዋጅ መሠረት፣ ቀደም ሲል በትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ይከናወኑ የነበሩ ተግባራት ለትራንስፖርት ቢሮ፣ ለመንገዶች ባለሥልጣንና ለትራንስፖርት ማኔጅመንት ማዕከል ተከፋፍለው ተሰጥተዋል።
በዚሁ መሠረት፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራዎች በትራንስፖርት ቢሮ ውስጥ እንደ አንድ ዘርፍ ሆነው በምክትል ቢሮ ኃላፊ ደረጃ እየተመሩ የሚከናወኑ ሲሆን፣ በመንገዶች ባለሥልጣን በኩልም የመንገድ ደህንነትን ማስጠበቅ፣ የትራፊክ ምልክቶችንና የፍጥነት መቀነሻዎችን ማስተዳደር፣ እንዲሁም የመንገድ አጠቃቀም ፈቃዶችን መስጠትን ጨምሮ ተያያዥ ሥራዎች እንዲከናወኑ ተደንግጓል።
የአዋጁ ዓላማ የትራፊክ ሥራዎችን ማቋረጥ ሳይሆን፣ በተለያዩ ተቋማት መካከል በግልጽ የተከፋፈሉ ኃላፊነቶችን በተቀናጀ መልኩ ማስፈጸም ነው።
ከአዋጁ ተግባራዊ አፈጻጸምና ከሥራ ርክክብ ሂደቱ ጋር በተያያዘ፣ ለጥቂት ቀናት የቁጥጥር ሥራዎች ላይ ክፍተቶች ተፈጥረዋል። በዚህም ምክንያት የፓርኪንግ ክፍያን አለመፈጸም፣ የፓርኪንግ አጠቃቀም ሥርዓትን መጣስ፣ እግረኞች መንገድ ሲሻገሩ ቅድሚያ አለመስጠት፣ በአንዳንድ የውስጥ መንገዶች የትራፊክ ሕግን የሚጥሱ ድርጊቶች መታየት፣ እንዲሁም ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ፍጥነትና የእንቅስቃሴ ሰዓት ውጪ መንቀሳቀስ ተስተውሏል።
እነዚህ ችግሮች በፍጥነት ሊታረሙ እንደሚገባ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የደረሱን አስተያየቶችም ያመለክታሉ።
በመሆኑም የሥራ ርክክብ ሂደቱ ተጠናቆ፣ የትራንስፖርት ቢሮ የቁጥጥር ሥራዎቹን በመደበኛው ሁኔታ ለማስቀጠል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል። ከነገ ጀምሮ የትራንስፖርት ቢሮ ኦፊሰሮች መደበኛ የቁጥጥር ሥራቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመተባበር የሕግ ማስከበርና የመንገድ ደህንነት ሥራዎችን ያጠናክራሉ። በበጎ ፈቃድ የትራፊክ ሥራዎችን ሲያግዙ የነበሩ በጎ ፈቃደኞችም አገልግሎታቸውን ይቀጥላሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ለሕብረተሰቡ ክብርና ጥቅም፣ ለፍትሐዊ አገልግሎትና ለመንገድ ደህንነት መጠበቅ ቅድሚያ ይሰጣል። በመሆኑም የትራፊክ ሕግን የሚጥስ ማንኛውም አሽከርካሪ፣ የቁጥጥር ሠራተኛ ወይም የሕግ አስከባሪ በሕጉ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል።
በመጨረሻም፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በተቀናጀ መልኩ እየተሰጠ መሆኑን ለሕብረተሰቡ እያረጋገጥን፣ ሁሉም የትራፊክ ሕጎችን እንዲያከብርና ለደህንነቱ እንዲተባበር ጥሪ እናቀርባለን።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.