አዲስ አበባ ከጠበቅሁት በላይ የተሻለች ሆና ተመልክቻለሁ- የአክራ ከተማ ከንቲባ
አዲስ አበባ ከጠበቅሁት በላይ የተሻለች ሆና ተመልክቻለሁ ሲሉ የአክራ ከተማ ከንቲባ ገለጹ፡፡
የአክራ ከተማ ከንቲባ ማይክል ክፓክፖ አሎቴይ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ የማይረሳ ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልጸው፣ በመዲናዋ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
ከንቲባው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በከተማዋ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች አድንቀዋል፡፡
በተለይም የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ጨምሮ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ የትምህርት ቤቶች እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በተቀናጀ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ የለውጥና የተስፋ ከተማ መሆኗን ቀደም ብለው ያውቁ እንደነበር በመግለጽ፤ በአካል ተገኝተው ያዩት ግን ከጠበቁት በላይ የተሻለ ሆኖ መመልከታቸውን አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ የተመለከቷቸውን መልካም ተሞክሮዎች ወደ ጋና በመውሰድ በአክራ ከተማ ተመሳሳይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች ትልቅ አርአያ መሆኗን ጠቅሰው፣ ከተማዋ በአሁኑ ወቅት እያከናወነች ያለችው የልማት ሥራ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ቢከናወን አህጉሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ ገልጸዋል።
የአክራው ከንቲባ፤ አዲስ አበባ ማንም ሰው ሊጎበኛት የሚገባ፣ አስደናቂ ውበት ያላት መሆኗን በመግለጽም፣ ሌሎች አፍሪካውያን እህቶችና ወንድሞች መጥተው እንዲጎበኙ መልእክት አስተላልፈዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.