አዲሱ መንግሥት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይመሰረታል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የመንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
አፈ-ጉባኤው በመልዕክታቸው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10 ሺህ 438 ዕጩዎች እንዲሁም ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተሳተፉበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ በስኬት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑንና ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ያስታወሱት አፈ-ጉባኤው፤ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀምር በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መደንገጉን አንስተዋል፡፡
እንደዚሁም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጥምር ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅና እንደሚመራ ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም መሠረት መስከረም 25 ቀን የመንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
ለሥነ-ሥርዓቱ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው፤ በሕዝብ የተመረጠው አዲሱ መንግሥት ቀጣዩን አምስት ዓመታት ሀገርና ሕዝብ የመምራት ኃላፊነት እንደሚረከብ አረጋግጠዋል፡፡
መጪው ዘመን የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የብልፅግና እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.