የዛሬን ኑሮ እያሻሻሉ የነገን ትውልድ የመገንባት...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የዛሬን ኑሮ እያሻሻሉ የነገን ትውልድ የመገንባት ስትራቴጂ በአዲስ አበባ

የኢትዮጵያ የልብ ምት የሆነችው አዲስ አበባ ባለፉት አምስት ዓመታት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት እና አስተሳሰብ በማሻሻል ወደ አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት ከተማዋ የምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ትውልድ ግንባታን ማጠንጠኛ ያደረገ "ሰው-ተኮር" ተግባር ነው።

የዚህ የለውጥ ጉዞ መሠረት አስተሳሰብን መለወጥ በመሆኑ ይህንኑ መርህ ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በተግባር እየተረጎሙት ይገኛሉ።

"ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ስንገነባ ልጆቻችን የሚረሱባት ከተማ ልትሆን አይገባም" በሚል ጽኑ አንድ ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ መርሐ ግብር መተግበሩ የዚሁ ስኬት ማሳያ ነው።

ከዚህ ቀደም በከተማዋ የመንግሥት የሕጻናት መዋያ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ያልነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸውን ከ1 ሺህ 100 በላይ ማድረስ ተችሏል።

በተጨማሪም የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ከ20 ወደ 5 ሺህ 500 ከፍ መደረጋቸው አስተዳደሩ ለትውልድ ግንባታ የሰጠውን ልዩ ትኩረት በጉልህ ያሳያል።

ይህ ሰው-ተኮር የልማት አቅጣጫ በትምህርት ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። አቅመ ደካሞችን ታሳቢ ያደረጉ የቤት እድሳት እና ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ለነዋሪው ምቹ የሆኑ ዘመናዊ መዝናኛ ስፍራዎች እና ፓርኮች ግንባታ፣ እንዲሁም የጤና ተቋማት ማስፋፊያ ስራዎች የዚሁ ትውልድን የመቅረጽ እና የዜጎችን ክብር ከፍ የማድረግ የተቀናጀ ራዕይ አካል ናቸው።

አስተዳደሩ በቀጣይ ዓመታት የትምህርት ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን ተደራሽነትን፣ ጥራትን እና ፍትሃዊነትን በዋና ምሰሶነት ነድፎ እየሠራ ነው።

ከንቲባዋ እንደገለጹት የስኬት መለኪያው በፈተና የሚያልፉ ተማሪዎች ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ የተማሪዎችን እውነተኛ "ልቀት" ማረጋገጥ ነው።

ዘንድሮ በ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና የተመዘገበው የ96 በመቶ የማለፍ ምጣኔ እጅግ አበረታች ቢሆንም፣ የከተማ አስተዳደሩ ዋነኛ ግብ ከዚህ የዘለለ መሠረታዊ እና ዘላቂ የጥራት ለውጥ ማምጣት ነው።

ትምህርት ቤቶችን ከአዋኪ ድርጊቶች ሙሉ ለሙሉ ነጻ በማድረግ ጤናማ የመማር ማስተማር አካባቢን በመፍጠር ረገድ የተከናወነው ተግባር ሌላው ስኬት ነው።

ተማሪዎች በስጋት ሳይሆን በተረጋጋ መንፈስ እንዲማሩ የትምህርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ አቅርቦትን በነጻ ማሟላት ተችሏል።

በተጨማሪም ተማሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ በመገደብ ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ከወላጆች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም ያለ መምህራን ብቃት የታለመውን ልቀት ማምጣት ስለማይቻል የመምህራንን አቅም መገንባት እና ጥቅማጥቅሞችን ማሻሻል ቀዳሚ ተግባር ሆኖ በመተግበር ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያካሄደ ያለው የለውጥ ጉዞ በመንግስትና በሕዝብ መካከል በተፈጠረ ጠንካራ የጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ነው።

ከተማዋ በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና መሰረተ ልማት ዝርጋታ እያስመዘገበች ያለው ስኬት በቀጣይ ዓመታት ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ትልቅ አቅም የሚፈጥርና በአፍሪካ ደረጃም የከተማነት ተምሳሌት ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.