ጳጉሜ 4 የህብር ቀን
ጳጉሜ 4 የህብር ቀን፦ በአድዋ ድል መታሰቢያ ከ50 ሺህ በላይ የማርሻል አርት ቤተሰቦች የተሳተፉበት ታላቅ ፌስቲቫል ተካሄደ
«ህብር የማርሻል አርት ፌስቲቫል» በሚል መሪ ቃል ዛሬ ጳጉሜ 4 ቀን እየተከበረ የሚገኘውን የ"ህብር ቀን" ምክንያት በማድረግ፣ ከ50 ሺህ በላይ የማርሻል አርት ቤተሰቦች የተሳተፉበት ታላቅ የህብር የማርሻል አርት ፌስቲቫል በአድዋ ድል መታሰቢያ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።
በፌስቲቫሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘውዱ ከበደ እንደገለጹት የህብር ቀንን ስናከብር ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቀለም እና ቋንቋ ሳይለያየን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክሩና የጋራ በሚያደርጉን የውል ትርክቶች ላይ በማተኮር ነው ብለዋል።
የማርሻል አርት ቤተሰቡ በስፖርቱ ያሳየውን ወኔ እና ህብረት በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በመድገም የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ማድረግ እንደሚገባ ኃላፊው አስገንዝበዋል።
አያይዘውም የጳጉሜ ቀናትን በተለያዩ ስያሜዎች ስናከብር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተሰሩ ውጤታማ ተግባራትን ከመዘከር ባለፈ በቀጣይ ዓመታት የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በታላላቅ የልማት እቅዶችና ራዕዮች የምንነሳሳበት መሆኑን አቶ ዘዉዱ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ በበኩላቸው፤ የህብር ቀን ዋና እሴት የሆነውን ህብረ ብሔራዊ አብሮነትና ስነ-ምግባር በመዲናዋ ስፖርት እድገት ውስጥ ማንጸባረቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት አዲስ አበባን የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ባሻገር፣ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች በስፖርቱ በመሳተፍ በስነ-ምግባር የታነጹ፣ ጤናማ እና አምራች ዜጋ የማፍራት ስራዉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም የህብር ቀን ሁላችንም ብዝሃነትንና ህብረ-ብሔራዊነትን አንድነታችንን በአብሮነታችን የምናደምቅበት ልዩ ቀን በመሆኑ ልንኮራበትና ልንደሰትበት የሚገባ አኩሪ እሳታችን ነዉ ሲሉ በእለቱ የስፖርቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
አክለዉም የማርሻል አርት ስፖርት አካላዊ ጥንካሬን ከመስጠት ባለፈ የውስጥ ዲሲፕሊን፣ መከባበርና አብሮነትን እንደሚያስተምር የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ ይህን የህብር ቀንን በጋራ ማክበራቸው ህብረተሰቡ ለጋራ ሀገራዊ ልማትና ሰላም በአንድነት ለመቆም የላቀ ሚና ያለዉ መሆኑን ጠቁመዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.