ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ አዲስ አበባ- የ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ አዲስ አበባ- የዓለም አቀፍ ሽልማቶች ሚስጥር

አዲስ አበባ ያሸነፈቻቸው የዓለም አቀፍ ሽልማት ዋነኛ ሚስጥር የሚገኘው ከመሠረተ ልማትና ውጤታማ  ስራዎች ብቻ ሳይሆን፣ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ ለማድረግ አጠቃላይ የሁለንተናዊ ብልፅግና ጉዞ ማዕከል በሆነው የሰብዓዊ ልማት እና ትውልድን በማነጽ ላይ በሰራችው ስር ነቀል ለውጥ ጭምር ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም”ን በብቃት በመምራታቸው በዓለም አቀፉ “አክት ፎር ኤርሊ ይርስ” (Act For Early Years) ኢኒሼቲቭ “የቅድመ ልጅነት ዕድገት ሻምፒዮን” ተብለው ተሸልመዋል። ይህ ትልቅ እውቅና ከተማዋን ለህፃናት የምትመች ከተማ እና ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ መዲና ለማድረግ የሰነቀችውን ራዕይ የሚያንፀባርቅ፣ እንዲሁም ለትውልድ ግንባታ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ያመጣውን ለውጥ በጉልህ የሚያሳይ ነው።

የዚህ ስኬት እና የከተማዋ አስደናቂ እድገት ማሳያ የሆነው ከቁጥር በላይ የሆነው መረጃ የመጫወቻ ስፍራዎች እና የሕፃናት ማቆያዎች መስፋፋት ነው።  20 የመጫወቻ ስፍራዎች ብቻ የተነሳው የከተማዋ አስተዳደር በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 5 ሺህ 500 ማድረስ ችሏል። በሌላ በኩል 5 ሺህ 3 የሚሆኑት የልጆችን የዕድገት ደረጃና ሥርዓት ታሳቢ ያደረጉ የመጫወቻ ቦታዎችም ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በተጨማሪም የሕዝብ የሕፃናት ማቆያዎች ከ11 ብቻ ተነስተው በአሁኑ ሰዓት 1 ሺህ 100 ደርሰዋል። ይህ በተለያዩ ሞዴሎች የተደራጀው የማቆያ ቁጥር በጥቅሉ 1 ሺህ 155 የደረሰ ሲሆን፣ 27 ሺህ 302 ሕፃናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

 ይህ ስኬታማ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በመዲናችን የሚገኙ 1.3 ሚሊዮን ገደማ ሕፃናትን፣ በተለይም 330 ሺህ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ታዳጊዎች ተደራሽ ለማድረግ ያለሙ አምስት አንኳር ጉዳዮችን ያካተተ ነው።

አዲስ አበባ ዛሬ አለምን ያስገረመችው እና የትኩረት ማዕከል የሆነችው በውብ የኮሪደር ልማቷ፣ በወንዝ ዳርቻዎቿ ውበት፣ ወይም በሌሎች ፕሮጀክቶቿ ብቻ አይደለም። ብሩህ አእምሮ ያለው ጤናማ ትውልድ በማፍራት፣ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ መሆኗን በተግባር በማሳየትና የዜጎችን በተለይም የሕፃናትን ሕይወት በሚቀይር የሰብዓዊ ልማት ሥራዋ ጭምር ነው። ይህ በሰብዓዊነት እና በትውልድ ላይ የተደረገው ጥልቅ ኢንቨስትመንት የመንግስትን የመደመር እሳቤ መሬት ያወረደ፣ ዜጎችን በአንድነት አስተባብሮ ከተማዋን እውነተኛ የብልፅግና ተምሳሌት ያደረጋት ሲሆን፣ ተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እንድትቀዳጅ ያስቻላት ዋነኛ ሚስጥርም ይኸው ነው።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.