ከመኪና ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሕግ ጥሰቶች የሚፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው - የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
በመዲናዋ በመኪና አስመጪዎች እና በኮሚሽን ሠራተኞች በኩል የሚፈጸምን የታክስ ስወራ እና የግብር ማጭበርበር ድርጊት ለመግታት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው፣ በርካታ የመኪና አስመጪዎች ለከተማ አስተዳደሩ የሚገባውን ወርሃዊ ቫት እና ዓመታዊ ግብር ላለመክፈል ሲሉ ሽያጮቻቸውን በኮሚሽን ሠራተኞች አማካይነት እያካሄዱ ይገኛሉ።
በተጨማሪም አብዛኞቹ አስመጪዎች አድራሻቸው ሳይታወቅ ከዋጋ በታች ደረሰኝ በመቁረጥ ከፍተኛ የግብር ስወራ ወንጀል እንደሚፈጽሙ በተካሄደው ጥናት መረጋገጡ በመግለጫው ተጠቅሷል።
በታክስ ሕጉ መሠረት በሌሎች ክልሎች የተመዘገቡ አስመጪዎች አዲስ አበባ ውስጥ ሽያጭ ለማካሄድ በሚያስችል መልኩ የክልል ንግድ ፈቃዱን ማስጠቀስ፣ የመሸጫ ቦታ መከራየት እና የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖቻቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።
ማንኛውም አስመጪ ያስገባውን መኪና መሸጥ ያለበት በኮሚሽን ሠራተኞች አድራሻ ሳይሆን ንግድ ፈቃድ ባወጣበት ቦታ ብቻ ሊሆን እንደሚገባም ቢሮው አሳስቧል።
የኮሚሽን ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሠራተኞችም ቢሆኑ በኮሚሽን ፈቃድ የመኪና መሸጫ ግቢዎችን ተከራይተው ከአስመጪዎች የተረከቧቸውን መኪኖች መሸጥ በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ የታክስ ስወራ ወንጀል መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ጥሪ ቀርቧል።
ቢሮው ከመኪና ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሕግ ጥሰቶችን የሚፈጸሙ አካላት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሕግ የማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.