በአዲስ አበባ የዜጎችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በአዲስ አበባ የዜጎችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመው "6400 A" የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለማቃለል የሚያስችለውንና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ የሚሳተፉበትን “6400 A” የተሰኘ የዲጂታል በጎነት ፕላትፎርም በይፋ አስጀምሯል።

ፕሮጀክቱን በይፋ ያስጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በከተማችን ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የበርካታ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንባ ያበስንበት የማህበራዊ ልማት ፕሮግራም መሆኑን ገልፀዋል።

የዲጂታል ፕላትፎርሙ ሀብትን ከብክነት በመታደግና ለታለመለት ዓላማ በማዋል የበርካታ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ማቃለል የሚያስችል መሆኑን አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።

የከተማችን የልማት አቅጣጫ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው በድህነት መኖር ተፈጥሯዊ ስሪታችን ባለመሆኑ የጋራ ችግራችንን ተባብረን መፍታት እንዳለብን አፅንዖት በመስጠት የከተማችን ነዋሪ በዚህ ዲጂታል ፕላትፎርም ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ በበኩላቸው በአዲስ አበባ የዜጎችን የኑሮ ጫና የሚያቃልሉ ዘርፈ ብዙ ግቦች ተቀርፀው በውጤታማነት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ከእነዚህ ግቦች መካከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጎነት የከተማዋ ዋና መገለጫና የህብረተሰቡ እሴት እንዲሆን በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ያወሱት ኮሚሽነሩ የ6400 A ዲጂታል በጎነት ፕሮጀክትም በለውጡ ዓመታት የተገኙ ሰው ተኮር ውጤቶችን ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።

ዜጎች በዚህ ፕሮጀክት ላይ ወደ 6400 "A"ን በመላክና በቀን 1 ብር በመለገስ ከተማ አስተዳደሩን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግብ ማሳካት እንደሚጠበቅ በመድረኩ ተገልጿል።

"በጎነት ለአዲስ አበባ ከፍታ!"


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.