አዲስ አበባ እንደ አዲሲቷ ሲንጋፖር

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

አዲስ አበባ እንደ አዲሲቷ ሲንጋፖር

የአንድን ከተማ ዕጣ ፈንታ ለመቀየር፣ ከፍ ያለ ራዕይ እና ከብረት የጠነከረ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያላቸው የለውጥ መሪዎች ያስፈልጓታል። 

የዚህ ዓይነተኛ ማሳያ የምትሆነው የእስያዋ የኢኮኖሚ ሞተር ሲንጋፖር ናት። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ሲንጋፖር ረግረጋማ፣ ድህነት ያንገላታት፣ የተበላሸ መሠረተ ልማት የነበራት እና ተስፋ የተቆረጠባት ደሴት ነበረች። 

ነገር ግን በሪፎርሚስቱ መሪ ሊ ኳን ዩ ራዕይ፣ የከተማዋ አሮጌ ገጽታ ፈርሶ፣ ከሥረ መሠረቱ እንደ አዲስ ተገነባች። የሲንጋፖር የለውጥ ኃይል ከተማዋን ከጭቃ እና ከውድቀት አውጥቶ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ፣ የፋይናንስ ማዕከል፣ እና የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል አድርጓታል። 

ይህ ታላቅ የከተማ ትንሣኤ፣ ቆራጥ መሪዎች ራዕያቸውን ወደ ተግባር ሲቀይሩ ከተማን ብቻ ሳይሆን የሀገርን ታሪክ እንዴት መቀየር እንደሚቻል ለዓለም ያሳየ ሕያው ምሥክር ሆኖ ተመዝግቧል። 

ዛሬ ላይ፣ ይህንኑ የታሪክ እና የለውጥ ድግግሞሽ በእናት ሀገራችን እምብርት፣ አዲስ አበባ ላይ እያየነው ነው። "አዲስ አበባ የብልጽግና ተምሳሌት" በሚል የለውጥ መንፈስ፣ ከተማዋ የድሮ አሮጌ እና ጨርጫሳ ገጽታዋን አራግፋ፣ ፈርሳ እንደ አዲስ እየተሠራች ትገኛለች። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጀመሩት የለውጥ ንቅናቄ አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን "አዲስ አበባ" ለመሆን፣ ወደማይቀለበስ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ገብታለች። 

የሲንጋፖር መሪዎች አሮጌዋን ከተማ አፍርሰው ወደ ዓለም አቀፍ መዳረሻነት እንደቀየሯት ሁሉ፣ የኛዎቹም መሪዎች ጊዜያዊ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር፣ ሌት ተቀን በመረባረብ አዲስ አበባን አፍሪካዊት የቱሪዝም እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ አፍሪካዊት የኢኮኖሚ ሞተር እና የውበት ስበት ማዕከል እያደረጓት ነው። 

አሁን በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች፣ የወንዝ ዳርቻ ድንቅ ዐሻራዎች፣ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክቶች፣ እና ሰፋፊ የመንገድ መሠረተ ልማቶች የዚህ ትውልድ ተሻጋሪ ራዕይ አካል ናቸው። ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ንጹሕ፣ አረንጓዴ እና ምቹ ከማድረግ አልፎ፣ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች፣ ግዙፍ ኢንቨስተሮች እና ዲፕሎማቶች የሚመኙት ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው። 

እንደ ሲንጋፖር ሪፎርሚስቶች ሁሉ፣ አዲስ አበባን የሚመራው የለውጥ ኃይል ፈተናዎችን፣ ትችቶችን እና ጊዜያዊ ዘመቻዎችን በጽናት ተቋቁሞ፣ ከፍ ያለውን ትልቅ ምስል በማየት ከተማዋን ዳግም እያነጻት ይገኛል። 

የከተማዋ ዕድገት በመንገድ ማስፋፋት ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክር፣ እንዲሁም ከተማዋን ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ እና የስብሰባ መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችል ነው። 

ይህ የሪፎርሚስት መሪዎች የጋራ ርብርብ የሚያሳየው አንድ ትልቅ እውነት አለ፤ የትኛውም ታላቅ ከተማ በአጋጣሚ፣ በምኞት ወይም በዕድል የማይፈጠር መሆኑን። 

ራዕይ ያላቸው መሪዎች አሮጌውን አፍርሰው አዲስ በመሥራት፣ ከተማዋን ከዘመኑ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር በማስተሳሰር የዓለም ምርጥ ከተማን በእውን መፍጠር እንደሚችሉ በተግባር እያሳዩን ነው። 

አዲስ አበባ በእነዚህ የለውጥ ኃይሎች በፈጠሩላት አዲስ የልማት መዋቅር መሠረት፣ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲናነት ክብሯን ከኢኮኖሚ እና ከቱሪዝም ልዕልና ጋር በማዋሐድ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከዓለም ምርጥ ዐሥር ከተሞች ተርታ የምትሰለፍ የዓለም አቀፍ ስበት ማዕከል መሆኗ የማይቀር ታሪካዊ ሐቅ ነው። 

ማፍረስን እንደ ጥፋት ሳይሆን እንደ አዲስ ጅማሬ፣ እንደ ዳግም ውልደት የቆጠሩት የኢትዮጵያ ሪፎርሚስት መሪዎች፣ የነገዋን አዲስ አበባ የብርሃን ከተማ ለማድረግ የያዙት ቆራጥ አቋም በእርግጥም የሚያኮራ ነው። 

በመሆኑም ከነአሮጌው አስተሳሰብ አዲስ ከተማ እንደማይገነባ ሁሉ፣ አሮጌውን አፍርሶ በተግባር በመሥራት፣ አዲስ አበባ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ከተማ የመሆን ራዕይዋን አሳክታ፣ ለትውልድ የምትሻገር የአፍሪካዋ ሲንጋፖር ሆና እንደምትወጣ ምንም ጥርጥር የለውም።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.