እነሆ ዛሬም ሌላ አዲስ የላቀ የህክምና ማዕከል!!
ዛሬ በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ውስጥ ለታካሚዎች ዘመኑን የዋጀ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ “አዲስ የላቀ የህክምና ማዕከል” ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል።
ነባሩ ሆስፒታል በጣም በማርጀቱ ለታካሚዎች የማይመች መጨናነቅ የነበረበት፣ የነበሩት ኋላቀር የህክምና መሳሪያዎች ለታካሚዎች ብቻ ሳይሆን ለባለሙያዎቹም አገልግሎት ለመስጠት ጥራቱን ያልጠበቀና ምቹ ያልሆነ ነበር።
ይህንን አስከፊ ሁኔታ ታሪክ በማድረግ እጅግ ንፁህ ውብ የሆነ ባለ7 ወለል ህንፃ ገንብተን በይዘቱ የህክምና አገልግሎቶችን እጅጉን የሚያሻሽል፤ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የተሟሉለት ሲሆን በነባሩ ህንፃ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በአጥፍ የሚያሳድግ ማዕከል ነው።
በአዲስ የላቀ የህክምና ማዕከል የ2026 ምርቶች የሆኑ AI የሚጠቀሙ ዲጅታል ኤምአርአይ (MRI)፤ ሲቲስካን፣ የአልትራሳውንድ፣ ተንቀሳቃሽ ኤክስሬይ፣ በሰዓት 30,000 ሊትር የሚያመርት የኦክሲጅን ማምረቻ (Oxygen plant)፤ እንዲሁም ቀድሞ የነበረው የአስተኝቶ ህክምና አልጋ ከ147 ወደ 360 አድጓል፥ የኦፕሬሽን ክፍል ከ3 ወደ 7፣ የፅኑ ህክምና ክፍልም ወደ 19 አድጓል። በተጨማሪም ሰፊና የላቀ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ስታንዳርዱን ጠብቆ ተደራጅቷል። የሰራተኛ ማረፊያ ክፍሎች፣ ላይብረሪ፤ ዘመናዊ ቢሮዎች፤ መሰብሰቢያ አዳራሾች እና የሰራተኛ ካፍቴሪያ አገልግሎት ለታካሚዎች በሚመች መልኩ ተገንብቶና ተደራጅቶ ለአገልግሎት በቅቷል።
አዲስ አበባ ላይ ያለው የጤና አገልግሎት ፍላጐት በመንግስት ብቻ የማይሟላ በመሆኑ የግሉን ዘርፍ በመደገፍም ወደ ውጭ በመሄድ ይደረግ የነበረውን ህክምና በአገር ውስጥ የህክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉ፣ ዓለም በዘርፉ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የጀመርናቸው ሥራዎች ህያው ምስክር ናቸው።
አዲሰ የላቀ የህክምና ማዕከል በፍጥነትና በጥራት ተገንብቶ የነበረውን አገልግሎት በአጥፍ በማሳደግ የላቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ እንዲጠናቀቅ አብራችሁን የነበራችሁ፣ የተባበራችሁ፣ የገነባችሁ በራሴና በታካሚው ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.