ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰላምና ደህንነት፣ ኢኮኖሚ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የውጭ ግንኙነትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ የመንግሥትን አፈጻጸም እና የቀጣይ እቅዶች አብራርተዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ለማቆም የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና በክልሉ የሚታዩ አዳዲስ ውጥረቶችን እንዲሁም የክልሉን ሰላም ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አንስተዋል። በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች የሃይማኖት ወይም የብሔር ሳይሆኑ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጥቅም ሳቢያ የሚነሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ሕዝቡ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን በመቃወም ሃገራዊ ተቋማትን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት፣ ግብርና እና ቱሪዝምን ለማነቃቃት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በግብርና 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን፣ ዘርፉም 7.7 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል። በኢንዱስትሪ የማኑፋክቸሪንግ አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ማደጉን፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን እና በሀገር ውስጥ ምርትን በማስፋፋት እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ መቆጠቡን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 21 ሚሊዮን ተጓዦችን ማጓጓዙን፣ ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በሀገሪቱ መካሄዳቸውን እና የአገልግሎት ዘርፉ 9.8 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል። በጤና ዘርፍ፤ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት ከ4 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማደጉን፣ አዳዲስ ሆስፒታሎች መገንባታቸውን፣ የወባ መከላከል እና የክትባት ተደራሽነት መስፋፋቱን አብራርተዋል። በትምህርት፤ 35 ሺህ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች እና 35 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ኩረጃን ለማስወገድ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያሳያል። በመኖሪያ ቤት ዘርፍ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት 1.2 ሚሊዮን ቤቶች መገንባታቸውን እና በቀጣይ 1.5 ሚሊዮን ተጨማሪ ቤቶች ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመቋቋም፣ መጠቀም እና መግራት በተባሉ ሶስት መርሆች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው በማንኛውም ብሔራዊ ውሳኔ ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማንቀበል አስረድተዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሊደፈር እንደማይችልና ይህንን ለማስጠበቅ አቅም እየተገነባ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ማስፈን፣ ኢኮኖሚን ማሻሻል፣ በምግብ ራስን መቻል፣ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎትን ማሳደግ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት የተገኙ ውጤቶችን በመዘርዘር የቀጣይ ትኩረትም እነዚህን ስኬቶች በማስቀጠል ዘላቂ ልማትና መረጋጋትን ማጠናከር እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.