#የጠሚሩምላሾች "በዓለ ሲመት የለም"
“በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት መንግሥት ከ4000 በላይ የምክክር መድረኮችንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁን የብሔራዊ መግባባት ምእራፍ ተሻግረናል። ባንዳዎችንና ጽንፈኞችን የምናሸንፈው በተጠናክረ ውይይት ብቻ ነው።”
ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ
“ይህንን ሰፊ ሀገራዊ እድል በመጠቀም፣ ካለፉት እሰጥ አገባዎች ወጥተን በሰለጠነ መንገድ መወያየት ይኖርብናል። በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉትን አወንታዊ እሴቶች ይዘን እንቀጥል፤ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች ደግሞ ማንንም በማይጎዳ፣ የሁሉንም መብት በሚያከብርና አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ እናሻሽላለን።ዋናው መገንዘብ ያለብን ነጥብ፦ አሁን የምንመክረው የአንድን ጊዜያዊ ገዥ ፓርቲ ስህተት ለማረም ብቻ አይደለም። ይልቁኑ ለዘመናት የተከማቹ ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በጋራ ጠረጴዛ ዙሪያ ፈትተን፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚበጅ አዲስ ማህበራዊ ውል ለመፈረም ነው። ይህ ምክክር በመወያየት፣ በመነጋገርና በመተማመን እንዴት አብሮ መኖር ይቻላል ለሚለው ታሪካዊ ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ የምንሰጥበት ብቸኛው መንገድ ነው!”
የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ፦
የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ተራ የድርድር ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኘ ታላቅ የሰላም ውጥን ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊ ወገኖች በእኩልነት ቁጭ ብለው የተወያዩበት መድረክ ነበር። መንግስት ወታደራዊ የበላይነት ከጨበጠ በኋላ የተሸነፈውን አካል በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጦ መደራደርና መፈራረም ብቻ ሳይሆን፣ በችግር ውስጥ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎችን ቀርቦ በመደገፍ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል። በዚህ ስምምነት ምን ተገኘ ለሚሉ ወገኖች ቢያንስ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም መቻሉን እንደ ትልቅ ስኬት ማንሳት ይቻላል። በተጨማሪም ከ60 ሺህ ያላነሱ ታጣቂዎች የዲዲአር (DDR) ክፍያ ተፈጽሞላቸው ከሰራዊቱ እንዲቀነሱ የተደረገ ሲሆን፣ በርካታ እስረኞችና ምርከኞችም ተፈተዋል።
የሃይማኖት መቻቻልን በተመለከተ፦
ኢትዮጵያ በጋራ እሴቶች እና በተቋማት የምትገነባ ሀገር እንጂ በግጭት የምትፈርስ አይደለችም። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚከተላቸው እምነቶች የተቀራረቡ እና የሰላም ተምሳሌቶች ለመሆናቸው፣ በታሪክም አብረው የመኖራቸው እውነታ ለዚህ ምስክር ነው። ወቅታዊ ግጭቶች የሃይማኖት ወይም የብሄር ሳይሆኑ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅምን ለመደበቅ በነውጠኞች የሚቀሰቀሱ ናቸው። በመሆኑም ሀገርን በዘላቂነት ለማጽናት ህዝቡ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን በመመከት፣ እንደ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ያሉ የሀገር ህልውና ጠባቂ ተቋማትን በሰለጠነ መንገድ ማክበር እና መደገፍ ይገባዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ
የኢትዮጵያን ብልጽግና እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ መዋቅሩን በዘመናዊ መንገድ መቅረጽ እና ማሻሻል የሚያስችሏትን ስትራቴጂዎች ቀርጻ ወደ ተግባር ገብታለች። ግብርናን በቴክኖሎጂ በማዘመንና ቱሪዝምን በማስፋፋት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ፤ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር እና የግል ዘርፉን በማበረታታት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ችሏል። ይህ የኢኮኖሚ ለውጥ የዓለም አቀፍ ጫናዎችን የመቋቋም፣ እንቅፋቶችን ወደ ዕድል የመቀየር እና የራስን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር መርሆዎችን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
የጤና ጉዳዮችን በሚመለከት፦
የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረት አቅማችንን ከነበረበት 4 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ችለናል። ለአጠቃላይ መድኃኒት ግዢ 70 ቢሊዮን ብር፣ ለሕክምና መሣሪያዎች ግዢ ደግሞ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገናል። ባለፉት ወራት በርካታ ሆስፒታሎችን መርቀን ለአገልግሎት ያበቃን ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ወራት የሚመረቁ ሌሎች ተቋማት ይኖራሉ። ለግንባታ ሂደት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን የአልጋ አቅም በአንድ ሺህ ያሳደገው አዲሱ ሕንፃ ይጠቀሳል። በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ተደርገው የተሰሩ ናቸው። ቀጣዩ ትኩረታችን በውጭ ሀገራት የምናያቸውን ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችን በሀገራችን መገንባት ነው። በሌላ በኩል፣ የወባ በሽታን ለመቀነስ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት 14 ሚሊዮን አጎበር የተሰራጨ ሲሆን፣ በ3 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች ላይ ደግሞ የጸረ-ወባ ኬሚካል ተረጭቷል። በተጨማሪም፣ ቀደም ሲል የክትባት ተደራሽነት ባልነበረባቸው 58 ወረዳዎች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባት መስጠት ተችሏል።
የትምህርት ዘርፍ ጥራት እና ለውጦችን በተመለከተ፦
የትምህርት ዘርፍ ጥራትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው። ባለፉት ዓመታት ተማሪዎች በራሳቸው ተማምነው ፈተና የሚወስዱበት አሰራር ተተግብሯል፤ በዚህም የኩራጃ ባህልን ማስረቀት ተችሏል። ትምህርት ከታች ካልተሠራ ከላይ መሥራት ውጤታማ አያደርግም፤ ለመዋዕለ ህጻናት ማስፋፊያ በተሰጠው ትኩረት 35 ሺህ መዋዕለ ሕጻናትን መገንባት ተችሏል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ኩረጃን ለማስቀረት፣ ትምህርትን በቴክኖሎጂ ለማስፋፋት እየተደረገ ያለው ሙከራ ተስፋ ሰጪ ነው። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ደረጃቸውን የጠበቁ እጅግ አበረታች ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይና ሉዓላዊነትን በተመለከተ፦
ዓለም ሊካድ በማይችል ሁኔታ ተለዋዋጭ በሆነችበት በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ የውጭ ፖሊሲ እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር በስትራቴጂካዊ ራስን መቻል ላይ የተመሠረቱ ሦስት ዋና ዋና መርሆችን እንከተላለን፤ የመጀመሪያው መቋቋም ሲሆን፤ ይህም የውጭ ተጽዕኖዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ተቋማዊ አቅምን መገንባት ላይ ያተኩራል። ሁለተኛው መጠቀም ሲሆን፤ ይህም ማንኛውንም የሚያጋጥም ፈተና ወደ ስትራቴጂካዊና መልካም የልማት ዕድል የመቀየር ብቃትን ያካትታል። ሦስተኛው ደግሞ መግራት ሲሆን፤ ይህም ሀገሪቱ የራሷን ብሔራዊ አጀንዳ ቀርጻ ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በልበ ሙሉነት እንድትጋፈጥና እንድትመራ ያስችላታል። በእነዚህ ሦስት ምሰሶዎች በመመራት በማንኛውም ብሔራዊ ውሳኔያችን ላይ የትኛውንም የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት ፍጹም አንፈቅድም።
ከ100 በላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ጀምረዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ከ100 በላይ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች በይፋ ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስመልክተው በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ በሀገራችን ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በኮደርስ ሥልጠና ላይ በመመዝገብ በዚህም ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ ልማቱ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ዘርፉ ላይ እያመጣ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ለውጥ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሚገኝና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዩኒቨርሲቲ መዋቅርም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
አክለውም በተለይም በስታርት አፖች (አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች)፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገቢ አሰባሰብ እንዲሁም በአጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ቴክኖሎጂ ከፍተኛና ስትራቴጂካዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ግብርና እና የምግብ ሉዓላዊነትን በተመለከተ፦
በዘንድሮው የምርት ዘመን 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉ እንዲሁም ዘርፉ የ7.7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ፤ የኢትዮጵያ ግብርና እያሳየ ላለው መዋቅራዊ ሽግግር ግልጽ ማሳያ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተገበረው የ‘ሌማት ትሩፋት’ መርሃ-ግብር አስደናቂ ውጤቶችን ያስመዘገበ ሲሆን፣ በተለይም አቮካዶን ወደ ውጭ በመላክ ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃን መያዝ መቻሉ ለሀገሪቱ ተጨማሪ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት አስደናቂ ድል እንዲመዘገብ አስችሏል። ከዚህም በላይ ለረጅም ጊዜ በከባድ ድርቅ ይጎዳ የነበረው የቦረና ቀጣና ዛሬ በሰፊ የስንዴ ልማት ተሸፍኖ ማየት መቻሉ የስትራቴጂያዊ ግብርና ስራችንን ስኬታማነት ያረጋግጣል። ምንም እንኳ የዓለም አቀፍ ጫናዎች ቢበዙም፣ የማዳበሪያ እና የነዳጅ ዋጋ ቢንርም፣ በቁርጠኝነትና በጠንካራ ስራ በምግብ ራሳችንን ለመቻልና በአፍሪካ ላይ የተለጠፈውን የረሃብ ታሪክ ለመቀየር በተግባር እየሰራን እንገኛለን፤ ምክንያቱም ምርጫችን ለምኖ መኖር ሳይሆን ሰርቶ ማደር ነው!
ኢንዱስትሪን በሚመለከት፦
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ ይገኛል። አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ እንዲል ሰፊ ጥናቶች እና የድጋፍ ስራዎች ተከናውነዋል። ይህ እድገት ከነባሮቹ የኮምቦልቻ፣ የመቐለ እና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ አስር አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ከ80 በመቶ በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብ ተችሏል። በተጨማሪም የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ስትራቴጂ ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህም ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ብርጭቆ እና ሴራሚክስን የመሳሰሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ብቻ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ መቆጠብ ተችሏል። ዘርፉ እያስመዘገበ ባለው ፈጣን እድገትም በማዕድን ዘርፍ 24 በመቶ፣ በማኑፋክቸሪንግ 20.3 በመቶ እና በኢነርጂ ዘርፍ ደግሞ 23 በመቶ ጭማሪ ታይቷል። ለወደፊቱም ይህን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ ትኩረት የተደረገ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ የ12.7 በመቶ እድገት እና ከኢንዱስትሪ ምርቶች ኤክስፖርት የ1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.