የከተማ አስተዳደሩ የድሆችን ቤት የቀሙ አመራሮችን ከኃላፊነታቸው በማንሳት ተበዳዮችን ወደ ቤታቸው መለሰ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 5) የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ ወደ ጎን በመተው፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነዋሪዎችን ለዘመናት ከኖሩበት የቀበሌ ቤት ያፈናቀሉ 3 የክፍለ ከተማ እና 2 የወረዳ አመራሮችን ተጠያቂ በማድረግ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ አድርጓል።
ኃላፊነታቸውን ያለአግባብ የተጠቀሙ አመራሮች፣ የካንሰር እና የልብ ህመምተኛ የሆኑ አቅመ-ደካሞችን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎችን በውድቅት ሌሊት እና በማለዳ በፖሊስ እና በኮንስትራክሽን ወዛደሮች አስከብበው፣ ንብረታቸውን በትነው ጎዳና ላይ እንደጣሏቸው ተበዳዮች ተናግረዋል።
የወረዳው ነዋሪ የሆኑት እናት፣ ወልደዉ በተኙበት ፖሊስ ከቤታቸዉ አውጥቶ እንደስወጣቸዉ ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የካንሰር ታማሚ በበኩላቸዉ፣ ፖሊስ ልጃቸዉን ጭምር አስፈራርቶ ከቤት እንዳስወጣቸዉ ነዉ የተናገሩት።
ይህንኑ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበላይ ኃላፊዎች ጉዳዩን በአስቸኳይ አጣርተው፣ የተፈጸመው በደል በፍጥነት እንዲታረም እና ተበዳዮቹ በአስቸኳይ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ አድርገዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ሐሰን እንደገለጹት፣ "መንግስት ቤት ሰርቶ ለድሆች ይሰጣል እንጂ ከቤት ደሀ አስወጥቶ ራሱ የሚገባበት አመራር የለውም" በማለት በጥፋተኞቹ ላይ የማያዳግም ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንና ተጠያቂነቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ቤታቸው የተመለሰላቸው እና ፍትህ ያገኙት ነዋሪዎችም ለከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ለከተማው አስተዳደር ምስጋና አቅርበዋል።
በከንቲባ ጽሕፈት ቤት የመልካም አስተዳደር ቅሬታና አቤቱታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባይነህ አመርጎ፣ አመራሩ የህዝብ አገልጋይ እንደመሆኑ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል አለበት ያሉ ሲሆን፣ ህብረተሰቡም መሰል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ለከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የምንኖረውም ህዝብ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን፣ ስናጠፋም መልካም ስንሰራም ህብረተሰቡ በቅርበት ይከታተለናል ያሉት አቶ አባይነህ፣ ሁሉም አመራር ይሄን ተረድቶ በተሰጠው ኃላፊነት ህዝብን በቅንነት ማገልገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.