በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን በሁሉም ክፍለ ከተሞች 11 (አስራ አንድ) ማዕከላትን እውን በማድረግ ቃላችንን በተግባር አሳይተናል !
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ግልፅ፣ ከአድሎና ጉቦ የፀዳ ፍትሃዊ አገልግሎት በሁሉም አካባቢ ማግኘት የሚያስችላችሁን ማዕከላት በማግኘታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ!
ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ሁለት አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ከፍተን በከተማችን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ11 (አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች) ማዕከላትን እውን አድርገናል።
በእነዚህ ማዕከላት ለህብረተሰቡ 50 በመቶ ያህል የመንግስት አገልግሎቶች እጅግ ቀልጣፋ በሆነ መልኩ እየተሰጠ ይገኛል።
ቀጣዩ ስራችን ደግሞ ቀሪዎቹን 50 በመቶ አገልግሎቶች ወደ እነዚህ ማዕከላት እንዲገቡ በማድረግ በአገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ በማዘመን ለነዋሪዎቻችን እርካታና እፎይታን መፍጠር ይሆናል።
ለረጅም ዘመን የተተበተበ ቢሮክራሲ፣ በብልሹ አሰራር ውስጥ የነበረውንና ለመለወጥ ጥረቶች ቢደረጉም ባለመለወጡ የሪፎርም ዝለትና ሊለወጥ አይችልም ወደሚል ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ የደረሰውን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ተግተን በመስራት ትልቅ ሽግግር ያደረግንበት፣ ህዝባችን ጊዜውንና ገንዘቡን ለልማት እንዲያውል በሚያደርግ ማዕከል መተካት ችለናል።
በሀገራችን ሙያተኞች የገነባናቸው እነዚህ ተቋማት የሀገራዊ ህልሞቻችን በለውጥ መገስገስ እንደምንችል ማረጋገጫዎች ናቸው ።የዛሬዎቹን ጨምሮ በአጭር ጊዜ በጥራት በመገንባት፣ በማማከር እንዲሁም ተቋሞቹን በቴክኖሎጂ እንዲሟሉ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ላደረጋችሁ ሁሉ በከተማችን ነዋሪዎች፣ በከተማ አስተዳደሩና በራሴ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.