በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዛሬ ሁለት ወር ያስጀመርነው የቅጠል ተራ የቤቶች ግንባታ በአስደናቂ ፍጥነት እየተሰራ ነው።
ዛሬ የቤቶቹን ግንባታ ሂደት በሳይቱ በመገኘት የገመገምን ሲሆን፣ የዛሬ ሁለት ወር የተጀመሩ ህንጻዎች 9ኛ ወለል ላይ መድረሳቸውን ተመልክተናል። ቦታውን ከማጽዳት ጋር በተያያዘ የዛሬ ወር የተጀመሩ ህንጻዎችም 4ኛ እና 5ኛ ወለል ላይ የደረሱ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት የግንባታውን ሂደት ተመልክተን የጨመርናቸው ሶስት ህንጻዎችም ጅማሮ በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል።
በፕሮጀክቶቹ የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የንግድ፣ የጸጥታ፣ ትምህርት ቤት እና ጤና ተቋማት፣ የስፖርት ማዘዉተሪያ፣ የህፃናት መጫወቻ እና የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች እንዲሁም ሌሎች የህዝብ የጋራ መገልገያዎች እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
በመሆኑም የምንገነባው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ህጻናት ቦርቀው የሚያድጉበት፣ ወጣቶች የአካል እና የአዕምሮ ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት፣ ዜጎቻችን አገልግሎቶችን በቅርበት የሚገኙበት እና ክብራችንን የሚያስጠብቅ ምቹና ፅዱ አካባቢን ነው።
በአጠቃላይ የቅጠል ተራ መኖሪያ መንደርን ትናንት ካስጀመርነው የገዳም ሰፈር እና በመሀሉ ላይ የሚገኘውን የጣልያን ሰፈር ጨምረን አገናኝተን በማልማት አካባቢውን የዘመነ አኗኗርና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር አካባቢ እናደርገዋለን።
በምርጫ ወቅት ላይ ሆነን የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሳይቀዛቀዝ መቀጠሉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቻችንን በታማኝነት የማገልገል አቋማችን ፅኑ መሆኑን ያሳያል።
ህንጻዎቹን በጥራት እና በፍጥነት ገንብተው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሰሩ የሚገኙ አመራሮቻችንን፣ ሰራተኞቻችንን፣ ማህበራትን፣ ተቋራጮችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.