ባለስልጣኑ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ያለአግባብ በኮሪደር ልማት ላይ የለቀቁ አልፎዝ ፕላዛ እና ሳሚ ህንፃ /800,000/ስምንት መቶ ሺህ ብር መቅጣቱን ገለፀ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13፣ ልዩ ቦታው ኢምፔሪያል አካባቢ የሚገኘውአልፎዝ ፕላዛ እና "ሳሚ ህንፃ" ከፍተኛ የሽንት ቤት ፍሳሽ ወደ ተገነባው የኮሪደር መስመር በመልቀቅ አካባቢውን በመበከላቸው አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣት ተቀጥተዋል።
ቅጣቱ የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው ደንብ ቁጥር 180/2017 (የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ) መሰረት፣ ህግ በመተላለፋቸው እያንዳንዳቸው 400,000 (አራት መቶ ሺህ) ብር በድምሩ 800,000 (ስምንት መቶ ሺህ) ብር የገንዘብ ቅጣት በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ።
የተወሰደው እርምጃ የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ እና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የወጡ ደንቦችን ለማስከበር የተጀመረው ጥብቅ ቁጥጥር አካል መሆኑ ተገልጿል።
ባለስልጣኑ ማንኛውም ተቋም እና ግለሰብ መሰል የብክለት ተግባራትን ከመፈጸም እንዲቆጠብ እና የወጡ ህጎችን እንዲያከብሩ ጥሪው አስተላልፏል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የደንብ መተላለፍ ድርጊት በሚፈፅሙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቋል።
ባለስልጣኑ መረጃውን ለሚሰጡት የህብረተሰብ ክፍል እያመሠገነ ሁሉም ነዋሪዎች ደንቡን ተላልፎ የሚገኝ አካል ሲመለከት በነፃ የስልክ መስመር 9995 ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አስተላልፏል።
መረጃው:- የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.