ኢትዮጵያ መርጣለች ፤ አሸንፋለች!
በየደረጃው የሚገኙ የከተማችን አመራሮች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተያዙ መንትያ ግቦችን ለማሳካት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ተግባራት ላይ ተግባቦት ፈጥረዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ህዝባችን ባራመደው ግልፅ አቋም፣ ከሌሊት እስከ ሌሊት በፅናት ድምፁን በመስጠት ባስተላለፈው ተግባራዊ መልዕክት ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆኗን አስገንዝበዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ፣ ጤናማ ፣ ገለልተኛ እና ሰላማዊ እንዲሆን የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት የምርጫ ስነ ምግባርን ባከበረ መልኩ አበረታች እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸውን አውስተዋል።
የሚዲያ ተቋማት ሀሳቦችን በሚዛናዊነትና በፍትሀዊነት በማስተናገድ ፣ የፀጥታ አካላት ገለልተኛ ሚናቸውን በመወጣት፣ ሲቪል ማህበራት ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን በማበርከት ጉልህ ሚናቸውን መወጣታቸውን ክብርት ከንቲባ ጠቁመዋል።
ምርጫው የኢትዮጵያውያንን የዴሞክራሲ ስርዓት መሻት እና ቁርጠኛ አቋም ለዓለም ማሳየቱን ያመላከቱት ክብርት ከንቲባ ለህዝባችን እና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውንና አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ከነበሩ ጥንካሬዎች በመማር ፣ ጉድለቶችን በማረም ፣ ሁሉንም አቅሞች በማስተባበር የህዝባችንን ጥያቄዎች በመመለስ፣ በአገልጋይነት መንፈስ እርካታውን በማሳደግ ህዝባችንን ለመካስ ብርቱ ርብርብ እንደሚደረግ ክብርት ከንቲባ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በተደረገው አበረታች ርብርብ ዓለም አቀፍ እውቅና ጭምር የተቸረው ስኬት መመዝገቡን አውስተዋል።
ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ የተሰጠው ልዩ ትኩረት በምርጫው ሂደትም መንፀባርቁን አቶ ጃንጥራር አስረድተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሰነድ ብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ መንትያ ግቦችን አስቀምጦ ፣ የምርጫ ቦርድን ህጎች ፣ አዋጅና መመሪያዎች ተከትሎ ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እና በፉክክር በመስራት ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የድርሻውን መወጣቱን አብራርተዋል።
ህዝባችን ከሌሊት እስከ ሌሊት በመሰለፍ ድምፁን በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ቀን ከሌት 7 / 24 መትጋትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.