የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተግባራዊ ፖሊሲዎች ለመደገፍ ያለመ አህጉራዊ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ያዘጋጀው ይህ ጉባኤ በአካዳሚክ ምርምሮች እና በፖሊሲ አፈጻጸሞች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላትን ታሳቢ ያደረገ ነው።
የአፍሪካ ልማትና የተግባራዊ መፍትሄዎች መድረክ (ADIF 2026) የሚል ስያሜ ያለው ጉባኤ “በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ተሞክሮዎችና የፈጠራ መፍትሔዎች” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው።
ጉባኤው በአፍሪካ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የወጣት ማኅበረሰብ፣ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አህጉራዊው ፍላጎትን ለመመለስ ከተያዘው ውጥን ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።
ይህ አዲስ መድረክ ከተለመዱ አህጉራዊ ስብሰባዎች በተለየ፤ የፖሊሲ አፈጻጸምን በማፋጠን በዘርፉ ያለውን የፖሊሲ እና የአሰራር ሂደት ለማቀለጣፈ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሠረት የኢኮኖሚክ ኮሚሽኑ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መሬት ያልወረዱ ጥናታዊ ምርምሮችን ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ በጥቂት አካባቢዎች ተሞክረው ስኬታማ የሆኑ አነስተኛ የሙከራ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት እንዲሁም አህጉር በቀል ምርጥ ተሞክሮዎችን በአገራት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ በቀጥታ ለማካተት አቅዷል።
አሠራሩ በልማት ላይ የሚፈሱ የአህጉሪቱ ኢንቨስትመንቶች አስተማማኝና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጡ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል።
የፎረሙን ውጤታማነትና ተጠያቂነት በተረጋገጠ መልኩ ለመከታተልም፣ ከጉባኤው በፊት፣ በጉባኤው ወቅትና ከጉባኤው በኋላ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል።
የመድረኩን ቀጣይነትና ትስስር አስተማማኝ ለማድረግ፣ የየዓመቱ መሪ ሀሳቦችን አንዱ ከሌላው ጋር በማስተሳሰር እና ተመጋጋቢ በማድረግ እንደሚዘጋጁ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በቀጣይ የሚካሄዱት ፎረሞች፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ትግበራን ከአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር ጨምሮ ሌሎች የልማት የትኩረት መስኮችን ታሳቢ በማድረግ እንደሚካሄድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.