በጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት 3 የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከላት ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በይፋ የመረቁት የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል ነዋሪዎችን ለዓመታት ሲያማርር ከኖረው የአገልግሎት አሰጣጥ እንግልትና ከብልሹ አሠራር የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች በማዕከሉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኮልፌ ነዋሪዎችን ከአገልግሎት አሰጣጥ እንግልትና ከሙስና የሚታደገው የመሶብ ዲጂታል ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስረዋል።
ይህ ዘመናዊ የዲጂታል ማዕከል ለአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ፣ የረጅም ጊዜ የሀገር ግንባታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነባ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚደርስባቸውን ውጣ ውረድ በማስቀረት፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሳያባክኑ የፈለጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች ቢሠሩም፣ አሁንም ድረስ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚታዩትን እንደ ፈጣን አገልግሎት አለመስጠት፣ እንግልት እና የእጅ መንሻ (ጉቦ) ጥያቄዎችን ከመዋቅሩ ውስጥ መንጭቆ ለማውጣት ማዕከሉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ነዋሪዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ያለምንም ጉቦ ማግኘት የሚችሉበትን አስተማማኝ ሥርዓት ይፈጥራል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተጀመረው ይህ የዲጂታላይዜሽን ንቅናቄ በዚህ ብቻ እንደማያበቃ የገለጹት ከንቲባ አዳነች ፣ ሦስት ተመሳሳይ የዲጂታል ማዕከላት የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት፣ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
ሕዝቡ በምርጫው ወቅት ያሳየው ታላቅ ፅናትና ፍላጎት፤ ሰላም፣ ልማት እና አጠቃላይ ሀገራዊ አካሄዶች በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲጓዙ መሻቱን በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዚህን ፅኑ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በሚመጥን መልኩ ምላሽ መስጠት፣ ሥልጣን ከሚይዘው አካል የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ተፅዕኖ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በራሷ ሕዝቦች፣ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማካሄዷ እና በምርጫው ማግስትም እንደነዚህ ያሉ ተጨባጭ ፍሬዎችን ማስመዝገቧ፣ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ወደ ከፍታ እንደሚመራ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ማሳያ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.