ለዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የምርት እጥረት እንዳያጋጥም እንዲሁም የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር ዝግጅት አድርገናል።
የከተማ አስተዳደራችን በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለ1145ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ ነዋሪዎቻችን በዓሉን ያለምንም የገበያ ጫና እና እንግልት በደስታ ማክበር እንዲችሉ፣ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እና የበዓል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ መጠን እንዲቀርቡ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።
በተለይም በከተማችን በሚገኙ 7ቱም የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት የሰብል፣ የጥራጥሬ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበው ይገኛሉ። ሸማቾች በቀላሉ በአቅራቢያቸው መገብየት እንዲችሉ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ 250 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ክፍት ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል። በ2,052 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች እና በአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት መጋዘኖች አማካኝነት የዘይት እና የዱቄት ምርቶች በበቂ መጠን ተደራሽ ሆነዋል።
በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች ከተጠቀሱት የገበያ አማራጮች በአቅራቢያችሁ ከሚገኙት መጠቀም ትችላላችሁ።
መልካም የዒድ አል-አድሃ በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.