የዓለም አቀፉ የሶሻል ሚዲያ ኮከብ ዲላን ፔጅ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎበኘ
በሚሊዮኖች ዘንድ “የዜና አባት” (News Daddy) በሚል መጠሪያነት የሚታወቀውና ከ19.3 ሚሊዮን በላይ የቲክቶክ ተከታዮች ያሉት ታዋቂው የእንግሊዝ ዲጂታል ጋዜጠኛ እና የይዘት ፈጣሪ ዲላን ፔጅ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጎብኝቷል።
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ “በቅኝ አገዛዝ ስር ወድቃ የማታውቅ ሀገር” በማለት ስለ ኢትዮጵያ ያለውን አድናቆት የገለጸው ዲላን፣ በመታሰቢያው በአካል ተገኝቶ ባየው እና በሰማው ታሪክ መደመሙን አሳይቷል።
በጉብኝቱ ወቅት የዓድዋ ድል መታሰቢያ አመራሮች ለዲላን ፔጅ ደማቅ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን፣ ታሪካዊውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሎጎ ያለባቸው ስጦታዎች ተበርክተውለታል፡፡
በመታሰቢያውም የኢትዮጵያን ቡና ጣዕም ለመቅመስ ችሏል።
ከዚህ ቀደም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ “በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀይረው የአፍሪካ የብርሃን ተስፋ” በሚል ርዕስ በሰራው ቪዲዮ የኢትዮጵያውያንን የአንድነት መንፈስ ለዓለም ያስተዋወቀው ዲላን፣ አሁን ላይ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና የሆነውን የዓድዋን ታሪክ በአካል መዘከሩ ለዲጂታል ዲፕሎማሲው ስኬት እና ለቱሪዝም ዘርፉ ማስተዋወቅ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
ይህ ታዋቂ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመታሰቢያው እና በሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ያደረገውን አስደናቂ ጉብኝት እና የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ በቀጣይ ቀናት ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ እንደሚያጋራ ይጠበቃል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.