መንግስታችን ለህዝብ የማይሰራውን ቃል አይገባም፤ የገባውን ቃል ይፈጽማል!
ዛሬም የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ ምርት በብዛት ማቅረቢያ እና የግብይት ማዕከላት ማስፋት ስራችን አካል የሆነውን 7ኛውን የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከልን ለአገልግሎት ክፍት እድርገናል።
የገበያ ማዕከሉ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ዘመናዊ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ ያላቸው 221 መጋዘኖች፣ የችርቻሮ ሱቆች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ በአንድ ጊዜ 250 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ፓርኪንግ፤ ለለሚ ኩራ፣ ለቦሌ እና የካ ክፍለከተሞች ነዋሪዎች አማካይ ቦታ በሆነው ሰሚት ዋና መንገድ ላይ የሚገኝ ምቹ የሆነ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ነው።
በገበያ ማዕከሉ ማህበረሰባችን ለዕለት ፍጆታ የሚጠቀምባቸውን የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ የበርበሬና የቅመማቅመም ምርቶች እና የኢንደስትሪ ምርቶች የአንድ ማዕከል የግብይት ስርዓት እውን አድርገናል።
በማዕከሉ የሚቀርቡ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የሚሸጥበት፣ ዋጋ የሚያንረውን ህገ ወጥ የደላላ ሰንሰለት በመበጣጠስ ከአምራቹ ያልተቋረጠ ምርት የሚቀርብበትና የከተማችን ነዋሪዎችን የኑሮ ጫናን የሚያቃልል ነው።
ከተለያየ ቦታ በኮሪደር ልማት የተነሱ ነዋሪዎችንና የገበያ ማዕከሉ ያረፈበትን 3.2 ሄክታር መሬት ለልማት የለቀቁልን አርሶ አደሮችም በማዕከሉ ሱቅ እንዲያገኙ አድርገናል ።
ለህዝብ የገባነውን ቃል በተግባር እንድናሳካ ጥረት ያደረጋችሁ የዲዛይንና የኮንስትራክሽን ስራዎች ቢሮ አመራርና ሰራተኞች፣ የንግድ ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች፣ የለሚኩራ ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ቦታው ለልማት እንዲውል ለሰጣችሁ አርሶ አደሮች በራሴ እና በከተማ አስተዳደራችን ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.