የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአዘርባጃን ባኩ ከተማ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ያደረገው ጉብኝት

ባኩ እጅግ ጽድት ያለችና ማራኪ ከተማ ናት። "ጥንታዊቷ ከተማ" (The Old City) በመባል የሚታወቀው የከተማዋ ክፍል በጥንቃቄ ታድሶ ለጉብኝት ክፍት ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም "ጥቁሯ ከተማ" (The Black City) ይባል የነበረውን አሮጌና ጎስቋላ ስፍራ፣ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማፍረስና እንደ አዲስ በመገንባት፣ አዲሲቷንና ውቢቷን ከተማ "ነጭ ከተማ" (White City-Baku) በሚል ስያሜ እውን ማድረግ ችለዋል።

ይህ የከተማ እድሳት ሂደት የእኛንም ተሞክሮ የሚያንፀባርቅ ነው። እኛም ታሪክንና ቅርሶቻችንን ጠብቀን እያደስን፣ ጎስቋላ አካባቢዎችን ደግሞ አፍርሰን በአዲስ መልክ በመገንባት ላይ እንገኛለን። ለአብነት ያህል፣ ቅርሶችን በማደስና ለቀጣዩ ትውልድ በማሻገር ረገድ፤ በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢ ያሉ ጥንታዊ ሕንፃዎችን፣ የመጀመሪያውን ሲኒማ ቤት፣ የመጀመሪያውን ማዘጋጃ ቤት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን እንዲሁም የተለያዩ ሐውልቶችን አድሰናል። ከዚህም ባሻገር እንደ ሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጎንደር ፋሲል ቤተ መንግሥት የመሳሰሉትን ታላላቅ ቅርሶች በማደስ ላይ እንገኛለን ።

በተጓዳኝም፣ እጅግ ጎስቋላና ለመኖር ምቹ ያልነበሩ መንደሮችን በማፍረስ ዘመናዊና ምቹ በሆነ መልኩ በድጋሚ ገንብተናል። በተለይም በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገራችን ከተሞች በተሳካ ሁኔታ የተተገበረው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የዚሁ የከተማ እድሳትና ማስዋብ ራዕያችን ዋነኛ ማሳያ ነው። በዚህም ስራ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ይበልጥ ምቹ፣ ማራኪ፣ አረንጓዴ እና ዘመናዊ ለማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ከማስፋት፣ ለእግረኛና ለብስክሌት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ከመፍጠር እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር አኳያ እጅግ አበረታችና ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቦበታል።

በአጠቃላይ ይህ የባኩ ጉብኝት፣ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የጀመርናቸውን የከተማ ልማት፣ እድሳትና የቅርስ ጥበቃ ስራዎች ይበልጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ተጨማሪ ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት ጠቃሚ ጉብኝት ነበር።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.