አዲስ አበባ የአፍሪካውያን የልማት አርአያነቷን እያረጋገጠች ነው- የ ቀዳማይ ልጅነት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ታዳሚዎች
በመዲናዋ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የ"ቀዳማይ ልጅነት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶች፣ አዲስ አበባ እያከናወነች ያለችው የልማት ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገለጹ።
ከተማዋን ተዘዋውረው የጎበኙት ታዳሚዎች እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረችበት ገጽታ ተላቃ በአሁኑ ወቅት ለዜጎቿ ምቹና ለጎብኝዎች ማራኪ ወደ መሆን ተሸጋግራለች።
ከዚህ ቀደም መዲናዋን ጎብኝተው የነበሩት እንግዳ እንደገለጹት፣ የአሁኗ አዲስ አበባ ከነበረችበት ሁኔታ ጋር ስትነጻጸር ሙሉ በሙሉ መለወጧን ገልጸዋል። "ዛሬ ያየኋት ከተማ ያኔ የነበረችው መሆኗን ማመን ይከብደኛል፤ ከፓርኮች ጀምሮ ከተማዋን ሰላማዊ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች በእጅጉ ያስደንቃሉ" ብለዋል።
ሌላኛው የጉባኤው ተሳታፊ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ላይ የታየው ለውጥ አፍሪካውያን ወደ አንድ መምጣት ቢችሉ ምን ያህል ሀያል መሆን እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል። "መሰረተ ልማቶቹ ግሩም ናቸው፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መጥተው የሚማሩባት የአፍሪካ መዲና መሆኗን በተግባር አረጋግጣለች" ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ረገድ እያከናወነች ያለውን ተግባር ከሲንጋፖር እድገት ጋር ያነጻጸሩት እንግዶች፣ በተለይም፤ የተፈጥሮ ሚዛንን የጠበቁ የልማት ስራዎች፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተሰጠው ልዩ ትኩረት፣እና የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን በመንግስት በኩል የታየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዛምቢያን ተሞክሮ ያነሱ እንግዳ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ክፍት ቦታዎችን ለዜጎች ምቾት በሚሰጥ መልኩ እንዴት ማልማት እንደሚቻል ትልቅ ልምድ የሚቀሰምባት ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። ከተማዋን ለመለወጥ የታየው የፖሊሲ ቁርጠኝነት ለሁሉም የአፍሪካ ከተሞች መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑም ተመልክቷል።
በአጠቃላይ፣ አዲስ አበባ ለዜጎቿ ምቹ ከመሆን ባለፈ፣ ለአህጉሪቱ አርአያ መሆን የሚችሉ የልማት ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን የጉባኤው ታዳሚዎች በአድናቆት አረጋግጠዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.