ለሕጻናት የምትመች ከተማ ለሁሉም ትመቻለች!
ዛሬ የመጀመሪያውን ዓለም-አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተከበሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በውቧ ከተማችን አስጀምረናል።
አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ዘርፍ የላቀ እና ተምሳሌት የሚሆን ተሞክሮ ያላት በመሆኗ፣ ይህን ዓለም-አቀፍ ጉባኤ ለማስተናገድ ተመራጭ አድርጓታል።
መንግስታችን በቀዳማይ ልጅነት ልማት ትርጉም ያለው ኢንቨስትመንት ማድረግ ምርጫ ሳይሆን የፓሊሲ ግዴታ አድርጎታል።
በመሆኑም በከተማችን ከ2025 ጀምረን “አዲስ አበባን ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ አልመን “ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ 1.3 ሚሊዮን ሕፃናት ተገቢ የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት እና ሁሉን-አቀፍ አገልግሎት ድጋፍ እንዲያገኙ ባለብዙ ዘርፍ ፕሮግራም ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን። በዋናነትም በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለ330,000 በኢኮኖሚ ተጋላጭ ቤተሰቦች ላይ ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው ።
እስካሁን በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ሕፃናት፣ ወላጆችና ቤተሰቦች የተቀናጀ ቀዳማይ ልጅነት ልማት አገልግሎት ተደራሽ አድርገናል፤ ይህም የመንግስታችን ለሰው-ተኮር ልማት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
በተለይም፣ ከ5,000 በላይ የወላጆች የአቅም ግንባታና ምክር ባለሙያዎችን አሰልጥነን ወደ ሥራ በማሰማራታችን አገልግሎቱን በቀላሉ ተደራሽ አድርጎታል፡፡
በ2015 በከተማችን 11 ብቻ የነበረዉ የህዝብ የሕፃናት ማቆያን በ2018 ወደ 1100 በማሳደግ የምግብ ፣ የህክምና፣ የስነ ልቦና የእንክብካቤ አገልግሎት በነፃ እየሰጠን ነው።
በተጨማሪም በ2015 በከተማችን 20 ብቻ የነበረዉን የልጆች መጫወቻ በ2018 ወደ 5000 በማሳደግ ልጆች ቦርቀዉ የሚያድጉበት አካባቢን መፍጠር ችለናል።
እየሰራናቸው ባሉት ስራዎች በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ ህጻናት መጠን በ2015 መርሃ ግብሩን ስንጀምር ከነበረበት 13% ወደ 10% ዝቅ ማድረግ የቻልን ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዝግጅታቸውም ከነበረበት 49% ወደ 90% ከፍ ማድረግ ተችሏል።
በጉባኤዉ ላይ አዲስ አበባ በዚህ ዘርፍ ያላትን ምርጥ ተሞክሮዎች አጋርታለች።
እንግዶቻችን በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እና የሀገራችንን እና የከተማችንን መስህቦች የሚጎበኙበት እንዲሆን እመኛለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.