‘’የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ በስራና ክህሎት ዘርፍ በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ስኬቶች አብራርተዋል። ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት በማድረግና ብቁ የሰው ሀብት እንዲሁም ምቹ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የተፈጠረባት ኢትዮጵያን ማየት የተለመው ይህ ዘርፍ፤ ከለውጡ በኋላ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የስራ ስመሪት እንዲሁም ዜጎች በቤት ውስጥ እና ባሉበት ሆነው በሚሰሯቸው ስራዎች አማካኝነት ለ19,872,846 ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።
ይህን ታላቅ ስኬት ለማስመዝገብ ያስቻለው፤ ኢንተርፕርነር ተቋማትን በመፍጠር፣ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር፣ የቢዝነስ መስፋፋት እና የልህቀት ማዕከላት በማሳደግ፣ ቲቬት ዲጂታላይዜሽን በማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች በመተግበራቸው የተገኘ ውጤት ነው።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በጤና ዘርፍ የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶችን ባቀረቡት ሪፖርት፦ ዘርፉ ከለውጡ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ካስመዘገባቸው ዋና ዋና ስኬቶች መካከል፤ ለ30 ዓመታት የቆየው የጤና ፓሊሲን በመከለስ፣ መከላከል ከሚለው መርህ በተጨማሪ አክሞ የማዳን ቁርጠኛ የፖሊሲ አመራር፣ የተቋም ግንባታ፣ የጤና መሠረተ ልማት ለውጦች፣ መድሃኒት፣ ክትባት እና የህክምና ግብዓቶች ምርት አቅርቦት እና ቁጥጥር ጭማሪ እንዲሁም የጤና ፋይናንስ እመርታ ቁልፍ እና ዋነኞቹ የለውጥ ስራዎች ናቸው።
በተለይም የወረርሽኝ ልየታ እና ቁጥጥር፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ የጤና ባለሙያዎችን ማብቃትና ቁጥራቸውን ማሳደግ፤ የዲጂታል ጤና፣ በዘርፉ የተተገበሩ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ግንባር ቀደም ስኬቶቿ ናቸው።
የጤና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ከፍ ያሉ እመርታዎች የተመዘገበበት አንዱና ዋነኛው መስክ ሲሆን ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተመርጣ ድርድሮችን እና ንግግሮችን እንድትመራ አስችሏታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶችን አቅርበዋል።
ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር። ዘርፉን በእጅጉ ተጭነውት ከነበሩ ችግሮች መካከል፤ የመሠረተ ልማት ጥራትና የግብዓት እጥረት፣ የተማሪ-መምህር፣ የተማሪ-ክፍል ጥመርታ አለመመጣጠን፣ ለትምህርት ዓይነቶች ብቁ የሆኑ መምህራን አለመኖር፣ የስርዓተ ትምህርት አግባብነትና የመጻህፍት ተደራሽነት ችግሮች፣ ኢ-ፍትሃዊነትና ኢ-እኩልነት፣ የትምህርት ሴክተሩ ትክክለኛነት መዳከም፣ ዝቅተኛ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መኖር ከብዙ ማነቆዎች ጥቂቶች ነበሩ።
በዚህም በጥናት በተደገፈ መልኩ፤ የትምህርት ዘርፉን ፍላጎቶች እና ተግዳሮቶች በመለየት ከተመዘገቡ ዋና ዋና ለውጦች መካከል፤ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ፣ የመፅሃፍት ህትመት ስርጭትና ተደራሽነት፣ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ማሳደግ፣ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሪፎርም፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ትምህርት መስፋፋት፣ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅትና አስተዳደር መሻሻል፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማደግ ዋነኞቹ በለውጡ ተግባራዊ የሆኑና ውጤት ያስገኙ ሆነው ተመዝግበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.