አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልቃድር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስረከቡ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለመጠበቅ እየተገበራቸው ባሉ የተለያዩ አማራጮች ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ተመርቀው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ቡዜና አልቃድር፣ በክፍለ ከተማው አስተዳደርና በከተማው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ትብብር የተገነባውን ጂ+3 የመኖሪያ ሕንጻ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል። ይህ ሕንጻ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥት አስተባባሪነትና በባለሀብቶች ተሳትፎ የተገነባ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚሁ የምረቃ መርሃ-ግብር ጎን ለጎን፣ በልማት ምክንያት ከመኖሪያቸው ለተነሱና በገላን ጉራ ሳይት ዕጣ ለወጣላቸው 25 የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ይፋዊ የቁልፍ ርክክብ ተከናውኗል። ለተነሺዎቹ የተላለፉት እነዚህ ቤቶች ሙሉ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟሉላቸው አካባቢዎች የተገነቡ፤ የነዋሪዎችን ሰብዓዊ ክብርና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸው ተመልክቷል።
አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልቃድር በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የከተማ አስተዳደሩ ከለውጥ ወዲህ በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ፈጣንና ጥራት ያለው እመርታ እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም ሁሉም በደስታ በሚያከብረው የበዓላት ወቅት ነዋሪዎችን ወደ አዲስ ቤት ማስገባት መቻሉ ልዩ እርካታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፣ በበዓሉ ዋዜማ የቤት ባለቤት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል ።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.