ሽንኩርት በኪሎ ከ25 ብር ጀምሮ በላፍቶ ሁለገብ ገበያ ማዕከል ማግኘት ይቻላል!
የትንሣኤ በዓል ገበያን ለማረጋጋት በትላልቅ የገበያ ማዕከላት ምርት በቅናሽ እየቀረበ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለፁ
በዚህም ሽንኩርት በኪሎ ከ25 ብር ጀምሮ እየቀረበ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል
ምክትል ከንቲባው በዛሬው እለት በላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል በመገኘት የበዓል ገበያ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
ምክትል ከንቲባው በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት በገበያ ማዕከሉ የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዲገቡ ቀደም ብሎ በተሰራው ዝግጅት መሠረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ድንች ያሉ ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህም ገበያውን ለማረጋጋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀው በላፍቶ ገበያ ማዕከል ለምሳሌ የሽንኩርት ምርት እንደየጥራቱ ከ25 ብር ጀምሮ እስከ 50 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ማዕከሉ ምርትን በጅምላ ተረክቦ ወደ ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ለማሰራጨት ያለውን ዝግጁነት ያሳያል።
ወቅታዊ ሁኔታዎችን ሰበብ በማድረግ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ ለመፍጠር ገበያ የተረጋጋ እንዳልሆነ አሉባልታ ለመንዛት የሚሞክሩ መኖራቸውን በመግለፅ ነጋዴዎችም ሆነ ሸማች ዛሬና ነገ ወደ ላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል መጥቶ መግዛት እንደሚችል አሳስበዋል
አልፎ አልፎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአቅርቦት ችግሮችንና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ "አጭበርባሪዎችን" ለመለየት የከተማ አስተዳደሩ ጥብቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል የሚገኙ ነጋዴዎች በበኩላቸው የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ምርት በስፋት እንዲገባ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ሰሞኑን ያለአግባብ ዋጋው ጨምሮ የነበረው የሽንኩርት ምርት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ እንዳሳየ ተናግረዋል።
ነጋዴዎቹ አክለውም በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ያለው የምርት አቅርቦት ከአዲስ አበባ ፍላጎት አልፎ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለክልሎችም የሚተርፍ በቂ ክምችት እንዳለም አንስተዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.