በአዲስ አበባ የትንሳኤ በዓል ገበያ፣ በተተመነ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በአዲስ አበባ የትንሳኤ በዓል ገበያ፣ በተተመነ ዋጋ ላይ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በአዲስ አበባ ከተማ ለትንሳኤ በዓል በተዘጋጁ የገበያ ማዕከላት ውስጥ በመንግስት ከተቀመጠው የዋጋ ተመን በላይ ሲሸጡ በተገኙ ሰባት የንግድ ድንኳኖች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በሚገኙ ስድስት የግብርና ምርት ማዕከላት፣ 246 የሰንበት ገበያዎች እና 11 ባዛሮች ላይ የንግድ ቢሮው የዋጋ ተመን አውጥቶ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል።

ኃላፊዋ እንዳሉት፣ በ8588 ነፃ የስልክ መስመር በኩል ከህዝብ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል፣ ሰባት የንግድ ድንኳኖች በተለጠፈው የዋጋ ተመን ሳይሆን ከዚያ በላይ ሲሸጡ ተገኝተዋል። በዚህም የተነሳ፣ ሰባቱም የንግድ ድንኳኖች ከስራ እንዲታገዱ ተደርጓል። እነዚህ ነጋዴዎች ዳግም መሰል የገበያ አማራጮችና ባዛሮች ላይ እንዳይሳተፉ ተወስኖባቸዋል።

ወይዘሮ ሀቢባ አክለውም፣ ከተማ አስተዳደሩ ሰፊ በጀትና ጊዜ መድቦ የሸማቹን ማህበረሰብ ጫና ለመቀነስ እየሰራ ባለበት ወቅት፣ እንዲህ ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን መፈጸም ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝበዋል። 

ድርጊቱን እንደ ሀገር ክህደት ነው የምንቆጥረው ያሉት ኃላፊዋ፣ ለህገ-ወጥ ነጋዴዎች ምንም ዓይነት ትዕግስት እንደማይኖርና ፈጣን እርምጃ መውሰዱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የንግድ ቢሮው ነዋሪዎች በማንኛውም የግብይት ሂደት ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ወይም ህገ-ወጥ ተግባር ሲያጋጥማቸው በ 8588 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል። እያንዳንዱ ጥቆማ በአግባቡ ተፈትሾ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
  https://linktr.ee/addisababacommunication


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.