ዛሬ መጪውን የትንሳዔ በዓል ምክንያት በማድረግ፤ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የአገር ባለውለታ አረጋውያንና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖቻችን ማዕድ አጋርተናል።
ይህ ተግባር በከተማችን የማዕከል መስሪያ ቤቶች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እየተከናወነ ያለ በጎ ተግባር ነው።
በሁሉም በዓላት የምናደርገው የማዕድ ማጋራት፤ ድጋፍ የሚሹ የከተማችን ነዋሪዎችን “ምን ጎደለ?" ብለን በመመልከትና በመጠየቅ ክፍተታቸውን የምንሞላበት ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የገለፅንበት ሰው ተኮር ተግባር ነው።
ማዕድ ከማጋራት ባለፈ አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ግጭትና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የሚከሰተውን ጊዜያዊ የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ ጉድለትን ለመሙላት፣ ከፍተኛ በጀት መድበን መሰረታዊ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያደረግን እንገኛለን። በዚህም የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በሰራነው ሥራ፣ በከተማችን የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲሰፍን ተደርጓል።
ወቅታዊ ችግሮችን ለመሻገር የምናከናውናቸው እነዚህ ተግባራት በሙሉ ከለውጡ ወዲህ የጀመርነው የ"ሰው ተኮር" ሥራዎቻችን አካል ናቸው።
አዲስ አበባ ለሀብታሙም ለድሃውም፣ ለሁሉም እኩል የተመቸች ፣ ስራዎቻችንም ማንንም ያልዘነጉ አካታች እንዲሆኑ እየሰራን ሲሆን፤ ከተማዋ እየተቀየረችና እየተለወጠችበት ያለው ልማት በሰዉ ኑሮና አኗኗር ላይ ለውጥ እያመጣ ያለ ነው።
"መስጠት አያጎድልም" ብለን ባደረግንላቸው ጥሪ መሰረት በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለሚደረገው ማዕድ ማጋራት ለተባበሩን ልበ ቀና ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻቸው ሁሌም እየተሸከሙ በጉልበታቸው በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ላሉ ወጣቶቻችን በሙሉ በራሴና በነዋሪዎቻችን ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተለይም ዛሬ በከንቲባ ፅ/ቤት ያካፈልነውን ያቀረቡልን Jospong Trading 15 ሚሊዮን ብር፣. አቶ ጀማል (ሚድሮክ) 10 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮዽያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን 7 ሚሊዮን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ (BKG) 5 ሚሊዮን ብር፣. አትሌት ዮሐንስ ቢፋ 2.9 ሚሊዮን ብር፣ አቶ ተካበ ሙሉ 500 ሺህ ብር በመለገሳቸዉ ከልብ እናመሰግናለን።
የትንሳኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ፍቅሩን እስከ መስቀል የገለጸበት እና በትንሳኤ የምስራች የተበሰረበት በመሆኑ፣ በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም፣ የአብሮነት ምክንያት እንሁን እያልኩ፣ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/addisababacommunication
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.