ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረ የዲፕሎማሲ ከፍታ፦ የ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረ የዲፕሎማሲ ከፍታ፦ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት የተከተለው ንቁና ስልታዊ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የሀገራችንን የውጭ ግንኙነት ለዘመናት በተዛባ መልኩ ይዞት ከነበረው “በጠላቶች የመከበብ እይታ” በማላቀቅ ለላቀ ዓለም አቀፋዊ ከፍታ የሚመጥን መሠረት ጥሏል።

በዚህም "ቅድሚያ ለጎረቤት" የሚለው መርህ ከቃላት ባለፈ በተግባራዊ ዲፕሎማሲ በመተርጎሙ ቀጣናዊ ግንኙነታችን ከጥርጣሬ አጥር ወጥቶ ወደ ጽኑ ስልታዊ አጋርነት ተሸጋግሯል።

የለውጡ መንግሥት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዋነኛ መለኪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው። ሀገራችን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የራሷን የሉዓላዊነትና የልማት ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት መርህን ስትከተል ቆይታለች።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙንን ዓለም አቀፍ ጫናዎች በብቃት በመቋቋም እና የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በማጠናከር እንደ BRICS አባልነት ያሉ የሀገራዊ ክብራችን ማሳያ የሆኑ ስኬቶችን አስመዝግበናል።

ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ዐቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የትስስር ማዕከል በመሆን በታዳሽ ኃይል፣ በመንገድ፣ በመጠጥ ውሃ እና በባቡር መሠረተ ልማቶች የቀጣናውን ሀገራት ዕጣ-ፈንታ ከራሷ ጋር አስተሳስራለች። ይህ የጋራ ዕድገት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ምሰሶ ብቻ ሳይሆን፣ የማይበገርና መሪ ቀጣናዊ ኃይል እንድትሆን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ አቅጣጫችን የመንግሥታችን ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ጽኑ ቁርጠኝነት መገለጫ ነው። ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ በህጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ በተለያየ መንገድ ከሀገር የወጡና ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ የተከናወኑ ተግባራት መንግሥት ለሕዝቡ ያለውን አለኝታነት ያሳዩና በዜጎች ዘንድ የላቀ ብሔራዊ ኩራትና መተማመንን የፈጠሩ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።

በዓለም ዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ተፅዕኖዋ እየጎላ እና ጥንካሬዋ እየጎለበተ የመጣው ሀገራችን አሁንም የፓን አፍሪካኒዝም ማማና የፅናት ተምሳሌት መሆኗን ለዓለም በድጋሚ ያረጋገጠ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ተገኝታለች።

ባለፉት ስምንት ዓመታት እንደሀገር የተመዘገቡት ስልታዊ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ከፍታ አሸጋግረውታል። ዛሬ ሀገራችን በውጭ ግንኙነቷ የምትታወቀው ድጋፍ በመጠየቅ ሳይሆን የቀጣናዊ አጀንዳዎች ምንጭና የመፍትሔ አካል በመሆን ነው። ይህ አዲስ ገጽታችንና እየተገነባ ያለው ብሔራዊ ኩራት ለሚገጥሙን ማናቸውም ጫናዎች እንዳንበረከክ አቅምና የልማት ጉልበት ሆኖናል።

የድላችን ጉዞ አይቆምም! ዜጎች ለተገኘው ውጤት ጠባቂ ለቀጣዩ ስኬት ደግሞ ባለቤት እንዲሆኑ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል።

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.