በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በስራ ሰዓት የእጅ ስ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በስራ ሰዓት የእጅ ስልክ መጠቀም ተከለከለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የግብር ከፋዮችን እርካታ ለማረጋገጥና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት፤ ከዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ሰራተኛ በመደበኛ የሥራ ሰዓት የእጅ ስልክ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን አስታወቀ።

የቢሮውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና በሪፎርም ስራዎች ውጤታማ ለመሆን እየሰራ የሚገኘው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፤ በዛሬው ዕለት በዋና መስሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከሚገኙ ከ7 ሺህ በላይ ሰራተኞቹ ጋር በስራ ሰዓት ስልክ አጠቃቀም ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ እንደተገለጠው፣ ቢሮው የአደረጃጀትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻያዎችን እያደረገ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ከግብር ከፋዮች ዘንድ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። በተለይም አገልግሎት ፈላጊን አስቀምጦ በግል የእጅ ስልክ መርበድበድ እና ለሥራ በተመደበ ኮምፒውተር የግል ጉዳዮችን መከታተል ዋነኛው የአገልግሎት መጓተት ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ ከመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ሰራተኛ በመደበኛ የስራ ሰዓት የግል የእጅ ስልክ መጠቀም የተከለከለ ሆኗል።

 ለሥራ አገልግሎት የተመደቡ ኮምፒውተሮችን ለግል ጉዳይ ማዋል በጥብቅ እንደሚታረም ስምምነት ላይ ተደርሷል። ሰራተኞች ማንኛውንም ግብር ከፋይ ያለ አድልዎና በቅንነት የማገልገል ግዴታቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩ የተገኙ ሰራተኞች በበኩላቸው፣ ከስልክ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት፤ አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግና ግብር ከፋዩን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ አዲስ መመሪያ የመንግስት ተቋማት ተገልጋይን ለማርካት ለሚሰሩት ስራ እንደ ትልቅ ማሳያ የሚወሰድ መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተመላክቷል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.