በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር እየተካሄደ ነው!
የመጀመሪያው የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ነው እየተካሄደ ነው።
የአዲስ አበባ ባህል ፣ ኪነጥበብ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሰርከስ ማህበር በጋራ ያዘጋጁት ይህ መርሐ ግብር ፣ “የሰርከስ ጥበብ ለኢትዮጵያ” ከፍታ በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 21 እስከ 24 ድረስ ይቆያል።
መርሃ ግብሩን የታደሙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ዘርፉን ከገፅታ ግንባታ ባለፈ ለኢኮኖሚ ፋይዳም ሰፋ አድርገን እየተጠቀምንበት ነው ብለዋል።
በከተማዋ የተከናወኑ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሰርከስን ጨምሮ ለኪነጥበብ ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብ እድገት እያሳየ መሆኑን የገለፁት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ድኤታ ረ/ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ ዘርፉ ኢትዮጵያን ገልጦ ለአለም እያሳየ መሆኑንና የውጭ ምንዛሬም እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰርከስ የመጭው ዘመን የኢትዮጵያ መገለጫ የጥበብ መስክ ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታው የእኛን የወል እውነትና ህብረብሔራዊነት በማንፀባረቅ ትልቅ የሀገር ገፅታ ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል።
ከተማ አሰተዳደሩ ባከናወነው የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋ የጥበብ ስራዎችን ለማከናወን ምቹ እንድትሆን ማስቻሉን ጠቅሰው፣ የከተማዋ መልካም የልማት ስራዎች በመላው ኢትዮጵያ ተስፋፍተው ጥበብ ጎልታ እንድትወጣ እያደረጉ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነጥበብ ቢሮ ሀላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) የሰርከስ ጥበብ የሀገርን ገጽታ ለማሳየት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የሰርከስ ጥበብን የወል እውነትና ህብረ ብሔራዊ ማሳያ በማድረግ ትልቅ የሀገር ገጽታ መገንቢያ እንደሚደረግ ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተክሉ አሻግሬ መንግስት ለዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው አዲስ አበባን የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ማዕከል ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.