ተልዕኮን በጀግንነት፣ ስፖርትን በውጤት” 2ኛው ከተማ አቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል በደመቀ ሁኔታ ተጠናቀቀ
ከመጋቢት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በ6 የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ከተማ አቀፍ የአዲስ አበባ ፖሊስ ስፖርታዊ ውድድርና ፌስቲቫል በዛሬው ዕለት ፍጻሜውን አግኝቷል።
በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማሎ ጀምበር ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፖሊስ ሰራዊቱ ከፀጥታ ጥበቃ ባለፈ ለሀገረ-መንግስት ግንባታና ለከተማዋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ስኬት ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል።
"የፖሊስ አባላት የሚከፍሉት መስዋዕትነት አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ደግሞ ሳቢ እንድትሆን አስችሏታል" ያሉት ዶ/ር ጀማሎ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴው በሰራዊቱ ውስጥ ጽናትንና የቡድን ስራን በማጠናከር ለላቀ አገልግሎት እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ሀይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ ውድድሩ የሰራዊቱን አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ዝግጁነት ከማሳደግ ባለፈ አዳዲስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ስፖርት የፖሊስና የህዝብ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር፣ የከተማዋን የብልጽግና ጉዞና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚያረጋግጥ የሰላም ዋስትና መሆኑንም አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው፣ ፖሊስን ከስፖርት ጋር ማቀናጀት ተቋማዊ ዲሲፕሊንና ብቃትን ለመገንባት ቁልፍ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ በርካታ የሀገራችንን ስም ያስጠሩ ጀግና አትሌቶች ከፖሊስ ተቋም የወጡ መሆናቸውን ያስታወሱት ዋና አዛዡ ይህ ፌስቲቫል ያንን ታላቅ ታሪክ የሚቀጥሉ ብቁና ዝግጁ የሆኑ የሪፎርም ውጤቶችን ለማፍራት የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ለሁለት ሳምንታት በቆየው በዚህ ውድድር በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስና በሌሎችም ስፖርቶች አሸናፊ ለሆኑ ቡድኖችና አባላት የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.