1447ኛው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በሠላም...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

1447ኛው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታና የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

1447ኛው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ስታዲየምና በከተማዋ በሚገኙ መስጊዶች የሚከናወነው የኢድ ሶላት ኃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በሠላም እንዲጠናቀቅ ጥምር የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታቋል። 

በመድረኩ የበዓል ጥበቃ የማስፈጸሚያ እቅድን መነሻ በማድረግ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለፀጥታ አካላቱ አመራሮች የስራ መመሪያ ተሰጥቷል። 

በከተማው የሚካሔዱ ህዝባዊና ኃይማኖታዊ እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች በሠላም እንዲጠናቀቁ ለማስቻል የፀጥታ ኃይሉ በልምድ የካበተ ውጤታማ ተሞክሮ ያለው መሆኑን ያስታወሱት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሸነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ የፀጥታ ኃይሉ ውጤታማ ተሞክሮውን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። 

አያይዘውም በበዓል መቃረቢያ ጊዜያቶች አንዳንድ ህገ-ወጦች የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና ከወቅታዊው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በተገናኘ ነዳጅ በኮንትሮባንድ እንዲሸጥ በማድረግ የዜጎችን ኑሮ በሚያከብዱ ግለሰቦች ላይ ጠንከር ያለ ህጋዊ ርምጃ መወሠድ እንዳለበት ገልጸው በዓሉን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ ስታዲየምና ወደተለያዩ መስኪዶች የሚመጡ ምዕመናን ለጋራ ደህንነት ሲባል ለሚደረጉ ፍተሻዎች ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ከተማዋ በፈጣን የዕድገት ጎዳና የምትገኝና ፍጹም ሠላማዊ መሆኗን ጠቁመው በተለይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚከናወነው የኢድ ሶላት ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትና በረከት በመሆኑ የተጠናከረ የጸጥታ ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው ከበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋርም ቅድመ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ መሠጠቱንም ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊና ኃይማኖታዊ ኩነቶች በሠላም እንዲጠናቀቁ በተከናወኑ የጸጥታ ጥበቃ ተግባራት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በዓሉ ኃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር በሁሉም እርከን የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮችና ነዋሪዎች ተወያይተው ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል። 

በዓሉ የሠላምና የደስታ እንዲሆን የተመኘው ጥምር የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ማንኛውም ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በነጻ የስልክ መስመሮች 990፣ 991፣ 987፣ 816 እንዲሁም በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በእጅ ስልኮች የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (Citizen Engagement Application) EFPApp በመጠቀም ጥቆማ መስጠት እንደሚገባም ጥሪውን ያስተላልፋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.