ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ የገነባነውን ዘመናዊ የጂ+4 የመኖሪያ ህንፃ፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ፣ለአካል ጉዳተኞች እና ለሀገር ባለዉለታ ለሆኑ ነዋሪዎቻችን "ቤት ለእምቦሳ" ብለን በክብር አስረክበናል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ
በተጨማሪም በተለያዩ የልማት ስራዎች የተነሱ በቀበሌ ቤት ውስጥ በደባልነት፣ በጥገኝነትና በላስቲክ ቤት ውስጥ እና የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በላያቸዉ እያለፈ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ወገኖቻችን ጭምር ቤት አስረክበናል ።
አዲስ ሰበባ በሰዉ ተኮር ስራዎቿ ተምሳሌት ሆናለች ። ሰዉ ተኮር ስራዎችን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀምረዉ በርትተን እንድንሰራ የስራ መመሪያ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፋት 7 አመታት በሰዉ ተኮር እሳቤችን እና በበጎነት አገልግሎት ተሳትፎ ከ45 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች መገንባት ችለናል።
በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በ4 ወራት አጭር ጊዜ ውስጥ የተገነባው ይህ የመኖሪያ ቤት፤ 5 ነባር ቤቶችን በማንሳት 70 አባወራዎችን ቤት እንዲገኙ ያደረገ ነው። ይህም ከእጦት መንፈስ ወጥተን ቦታን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚሳይ ሲሆን፣ በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ተገንብቷል። ግንባታው የጥራት ደረጃውን የጠበቀ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ የዜጎችን ክብር የሚመጥንና የቤት ቁሳቁስ የተሟላለት ዘመናዊ ህንፃ ነው።
ከተማችን ለሁላችንም ትበቃለች፤ መተሳሰብና ፍቅር ካለ ደግሞ ይበልጥ መስራት ይቻላል። በቀጣይም ለብዙዎች ለመድረስ በትጋት እንሰራለን።
ይህን እጅግ ዘመናዊና የዜጎችን ክብር የሚመጥን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማስተባበር ለተሳተፋችሁ ተቋማት፣ ባለሀብቶችን ላስተባበሩት የከንቲባ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ ፣ ለደገፋችሁ ባለሀብቶችና ድርጅቶች በሙሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.