የወርሃ ጥር እና የካቲት 𝟐𝟎𝟏𝟖 የስራ ትግበራዎ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የወርሃ ጥር እና የካቲት 𝟐𝟎𝟏𝟖 የስራ ትግበራዎች ማጠቃለያ፤

በሁለቱ ወራት ፈር ቀዳጅ የዲጂታል አገልግሎቶች፣ መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት እና የኢኮ-ቱሪዝም ልማቶች የተመረቁበት እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ዓለም አቀፍ ትብብሮች የተጠናከሩበት ነበር።
‎ 
‎የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ𝟔ኛው የሥራ ዘመን 𝟏𝟎ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች:-

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ጠቁመዋል። በሪፎርሙ ማግስት መንግሥት አንድም የንግድ ብድር ባለመውሰዱ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ከሸቀጥ ኤክስፖርት 5.1 ቢሊዮን ዶላር (የዕቅዱን 120 በመቶ)፣ ከአገልግሎት ዘርፍ 4.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከሬሚታንስ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ይፋ አድርገዋል። በቴክኖሎጂ ረገድም የአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ኢንስቲትዩት መቋቋሙን እና በዓለም ሁለተኛ የሆነው የኤአይ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ሊከፈት መሆኑን፣ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 97 ሚሊዮን እንዲሁም የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚዎች 58 ሚሊዮን መድረሳቸውን ገልጸዋል። ብሔራዊ ሰላምን በተመለከተ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ፣ የወልቃይት ነዋሪዎች በሰላም የመኖር መብት እንዳላቸው እና የትግራይ ሕዝብ በፖለቲካው መድረክ ዋና ተዋናይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል ።

‎መሠረተ ልማት እና የከተማ ትራንስፎርሜሽን:-
‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት ክንውኖችን በመጎብኘት እና በማስጀመር የሀገሪቱን የዘመናዊነት ጉዞ በተግባር ያረጋገጡበት ወር ነበር። በሀዋሳ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ የተመለከቱ ሲሆን፣ በነቀምቴ ከተማም ዘመናዊ የትራፊክ አስተዳደር እና ከመሬት በታች የሚዘረጉ የመሠረተ ልማት ሥርዓቶችን ያካተተውን የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተዋል ።

‎ግብርና፣ መስኖ እና የምግብ ሉዓላዊነት:-
‎የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዋና ዋና የግብርና ስፍራዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል። በ"ሌማት ትሩፋት" መርሐ ግብር በሀዋ ገላን ወረዳ የለማውን የሙዝ ክላስተር የጎበኙ ሲሆን፣ ለተለያዩ ሰብሎች አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት የሚሰጠውን የቄጦ መስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትንም ተመልክተዋል ። በተጨማሪም የአርጆ ዲዴሳ መስኖ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ የገመገሙ ሲሆን፣ በብላቴ ወንዝ አካባቢ በግል ባለሀብቶች እየለሙ ያሉ የፍራፍሬ ልማቶችን ጎብኝተዋል ። በቀን 2,000 ቶን በቆሎ የመፍጨት አቅም ያለው የቡሳ ጎኖፋ የተቀናጀ የምግብ ኢንዱስትሪ ግንባታንም በይፋ አስጀምረዋል ።

ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን
‎በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕግ ማስከበር ሥራን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሀገሪቱን የመጀመሪያ ሰው አልባ "ስማርት" የፖሊስ አገልግሎት አስጀምረዋል ። በኢንዱስትሪ ዘርፍ የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካን የጎበኙ ሲሆን፣ ይህም #ኢትዮጵያታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 66.3 በመቶ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት እና በግል ባለሀብቶች ጥምረት እየለማ ያለውን የቱሉ ካፒ ወርቅ ልማት ፕሮጀክትንም ጎብኝተዋል።
‎ 
‎ኢኮ-ቱሪዝም እና ዘላቂ ልማት:-
‎በ"ገበታ ለትውልድ" መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወሎ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሎጎ ሀይቅ ሪዞርትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል። በነቀምቴ ከተማ አቅራቢያ በ14 ሄክታር ላይ በፍጥነት እየተገነባ ያለውን የሶርጋ ኢኮ ሎጅንም ጎብኝተዋል። በተጨማሪም በምሥራቅ ወለጋ የመዴ ጃለላ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በመጎብኘት ዘመናዊ የፀሐይ ኃይል እና የባዮ ጋዝ ሥርዓቶች የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት እንዴት እየቀየሩ እንደሆነ ተመልክተዋል።

ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች:-
‎በዲፕሎማሲው ረገድ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ ባዘጋጀችበት ወቅት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጣሊያኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒን የተቀበሉ ሲሆን 39ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ሊታደሙ ከመጡ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችም ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱርክዬን ፕሬዝዳንት ረጀፕ ጣይብ ኤርዶዋንን እና የእስራኤሉን ፕሬዝዳንት ይስሐቅ ሄርዞግን በአዲስ አበባ ተቀብለው ስለ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቀጣናዊ መረጋጋት ጨምሮ በመጠነ ሰፊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዘርባጃን ባደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝትም ከፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር በመሆን የመከላከያ ትብብር ስምምነት፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ፣ በኢንቨስትመንት፣ በጸረ-ሙስና እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመዋል ።

ብሔራዊ ደህንነት እና ተቋማዊ ሪፎርም:-
‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ኦፕሬሽን ኮማንድ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በመገኘት ዘመናዊ የአየር እና የውሃ ላይ ወታደራዊ ትርዒቶችን ተመልክተዋል ። ኮማንዱ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ በዘመናዊ መልክ መዋቀሩን አድንቀዋል። በተጨማሪም የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባን በመምራት በቀጣይ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

#PMOEthiopia


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.