አምራች ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ቅድሚያ የምንሰጠ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

አምራች ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባር ነው፡- ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሀገር ግንባታ የላቀ ፋይዳ ያላቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት መደገፉን እንደሚቀጥል የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባው ይህንን ያሉት ''ኢትዮጵያ ታምርት አዲስ አበባ ትበልፅግ'' በሚል መሪ ሀሳብ ለሳምንት ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ ላይ ነው። 

አምራቹ ማኅበረሰብ የሚፈልገውን አገልግሎት የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ አመራሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

በከተማዋ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ወደ 3 ሺህ 900 ከፍ ማለቱንና የማምረት አቅም አጠቃቀምም 69.9 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

ባለፉት ሥድስት ወራት ብቻ በዘርፉ ለ58 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በተኪ ምርቶች አማካኝነት ከ849 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል። 

በተጨማሪም ከወጪ ንግድ ከ123 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ የዘርፉን ስኬት አጉልቶታል።

ከ230 በላይ አምራቾች በተሳተፉበት በዚህ ንቅናቄ፤ ውጤታማ ለሆኑና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ላስገኙ ባለሀብቶች የዕውቅና ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል። 

አምራቾች የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ለከተማዋ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡም ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.