ዛሬ በአዲስ አበባ ፖሊስ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት ዕለት ነው።
በመዲናችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማትን መርቀን በይፋ ሥራ አስጀምረናል። በዚህም የፖሊስ መምሪያዎች፣ ጣቢያዎች፣ ካምፖች እንዲሁም የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ተቋማት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።
ይህ ተግባር በከተማችን ፖሊሳዊና ድንገተኛ አደጋን የመከላከል አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ ደጃፍ ይበልጥ ከማምጣቱም በላይ፤ ነዋሪው በሰላም ግንባታና በአካባቢ ጥበቃ ሂደት ላይ በባለቤትነት ስሜትና በንቃት እንዲሳተፍ የሚያስችል ነው።
በተለይም እነዚህ ተቋማት በየአካባቢው መገንባታቸው ወንጀልን ለመከላከልና ድንገተኛ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የሚሰጠውን የምላሽ ጊዜ በእጅጉ በማሳጠር፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ።
ተቋማቱ መዲናችን ከደረሰችበት ፈጣን የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲመጣጠኑ ተደርገው ከመገንባታቸውም በላይ፤ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ አካታች መሰረተ ልማቶች ሲሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየባቸው፣ የሕፃናት ማቆያና ክሊኒክን ያካተቱ፣ እንዲሁም በዘመናዊ የመረጃ ማሰባሰቢያና የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎች የተደራጁ ናቸው።
እነዚህ ፋይዳቸው ጉልህ የሆኑ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ እውን እንዲሆኑ ላስቻላችሁ ባለድርሻ አካላት በሙሉ፣ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.