ሙስናን የመከላከል ትግል መላው ማህበረሰብ ፣ ሁሉም ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት ይገባል!
ዛሬ 22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት እና የገባነውን ቃል በማደስ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሙስናን የብልፅግናችን ፀር፣ የኢፍትሀዊነት ምንጭ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ያፋፋምነው ትግል ከዚህ ቀደም የነበረን አስከፊ መንግስታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት አስችሏል። በዚህም እንደ አገር ብሎም እንደ ከተማ የህዝብና የመንግስትን ሀብት በተገቢው የልማት ስራዎች ላይ በማዋላችን አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት ችለናል።
መንግታዊ / ስርአታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ብንችልም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚታይ በመንግስት ሃላፊዎች እና ሰራተኞ የሚፈፀመው ሌብነት እና ጉበኝነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋት እና ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር፣ መንግስታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆንና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል የሁሉንም ተቋማት ትግል እና የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል።
ቤተሰብ፣ ማህበረሰቡ፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት … ወዘተ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በፀረ ሙስና ትግል ውስጥ በአመለካከትም በተግባርም ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ።
በመሆኑም የፀረ ሙስና ትግላችን ይበልጡን ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ።
ፈጣሪ ኢትዮዽያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ !
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.