
የገዳ ስርዓት አካል የሆነው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በስኬት መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለፀ፡፡
በርካታ ታዳሚዎች፣ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ሀገር ዜጎችና ቱሪስቶች የታደሙበት "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል የተከበረው የዘንድሮ የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በአል በደማቅ ስነ-ስርዓት በስኬትና በሠላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
በያዝነው አዲስ ዓመት በርካታ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት ያከበራቸው ኃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ፍፁም በስኬት ተከብረው መጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀትና ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር አባገዳዎች፣ አደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ የከተማው ነዋሪ እንዲሁም በየእርከኑ የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ላደረጉት አስተዋፅኦ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት አመራሮችና አባላት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ስም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ጠቅላይ መምሪያው አያይዞ እንደገለፀው በነገው እለት በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በአል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ተቋማት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ተግባር የገቡ ስለሆነ ህዝቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.