.png)
በልደታ ክፍለ ከተማ የኢሬቻ በዓልን "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል በድምቀት ተከበረ።
"ሁሉም በዓሉን ሲያከብር የበዓሉን ወግ እና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚጠብቅ እና በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል!!- ወ/ሮ አለምፀሐይ ሽፈራው
የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊ ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራው፣ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ፣ የክ/ከተማው ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፍታለው ከፍያለው፣ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አራርሳ ድሪባ ጨምሮ የከተማ፣ የክ/ከተማ እና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቄሮዎች እንዲሁም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በመርሀ ግብሩ ላይ መልክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊ ወ/ሮ አለምፀሐይ ሽፈራው እንደገለፁት የኢሬቻ በዓል የተገኘውን ለውጥ ያስቀጠልንበት፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በእኩልነት የሀገር ማንሰራራት ጉዞ የጀመርንበት እና የዘመናት ቁጭት የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ የበቃበት በመሆኑ በዓሉን ድርብ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ አለምፀሐይ አክለው ኢሬቻ ከገዳ ስርአት አንዱ አካል በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት፣ እርቅ፣ ፍቅር፣ ሰላም የሚሰበክበት ጥልቅ የሆነ ፍልስፍና ያለው ታላቅ በአል መሆኑን አንስተዋል።
ሁሉም በዓሉን ሲያከብር የበዓሉን ወግ እና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚጠብቅ እና በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ወ/ሮ አለምፀሐይ አሳስበዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው የኢሬቻ በአል ፍቅር የሚሰበክበት፣ አንድነትና አብሮነት ጎልቶ የሚወጣበት፣ መተሳሰብ በእጅጉ የሚታይበት፣ መረዳዳትና ወንድማማችነት የሚጠናከርበት፣ ዓመቱ በሰላም ይጠናቀቅበት ዘንድ ምኞትና ምርቃት የሚካሄድበት በዓል ነው ብለዋል።
ወ/ሮ ልዕልቲ አክለው የኢሬቻ በዓል ከኢትዮጵያ አልፎ ብዙ የውጭ ሀገራት ዜጎች የሚታደሙበት ልንኮራበትና ይበልጥ ልናጎለብተው የሚገባ ባህላዊ እሴታችን ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በበዓሉ ዝግጅት ላይ የኢሬቻ በአል ታሪካዊ ዳራውን በስፋት ያነሱት ደግሞ የክ/ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አራርሳ ድሪባ ሲሆኑ ኢሬቻ በበዓሉ የተገኙት ሁሉ ይቅር የሚባባሉበት፣ ፀበኞች የሚታረቁበት፣ ቂምና ቁርሾ የሚተውበትና የተጣላ ይቅርታ የሚደራረጉበት ድንቅ የሆነ የሰላም ግንባታ ተምሳሌት በዓል ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ህዝብ የሚተዳደርበት የገዳ ስርዓት ለዘመናዊ ዴሞክራሲ መሰረት የሆነና ታናሽ ታላቅን አክብሮ ከታላቅ የሚማር፣ ታላቅ ደግሞ ታናሽን በማብቃት ስርዓትን የሚያስቀጥል ስርዓት ነው በማለት አቶ አራርሳ ጨምረው አብራርተዋል።
ዝግጅቱ በአባ ገዳዎችና ሀደ ሲንቆዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን ባሕላዊ ምግቦች፣ ባህላዊ ጭፈራዎች እና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ቀርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.